አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህግ የበላይነትና የህዝብን ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ግዴታውን ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በኢሬቻ በዓል በተፈጠረው ሁከት ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለማሰብ መንግስት ያወጀውን የሀዘን ቀን እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙ ያሉ ሀይሎች አሁንም የህዝብና የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል እየተሯሯጡ ይገኛሉ ብሏል።
በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የተፈጠረውን ሁከት ለመቆጣጠር ጸጥታ ኃይሉ ያደረገውን ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት በቀናነት መመልከት ካለመፈለጋቸውም በላይ መንግስት ከአየርና ከምድር በጥይት ዜጎችን ጨፈጨፈ የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የጥፋት ተግባራቸውን ቀጥለውበታልም ነው ያለው መግለጫው።
የጉዳቱ ሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የህክምና ተቋማት በገሃድ ያረጋገጡትን ሀቅ በማዛባትና የፈጠራ ወሬዎችን በመንዛት ህዝቡንና የአለምን ማህበረሰብ ለማደናገር ጥረት እያደረጉ እነደሚገኙም ጠቁሟል ።
እነዚህ ኃይሎች በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከበሬታ ያላቸውን አባገዳዎች በታላቁ ኢሬቻ በዓል መድረክ ሳይቀር ማዋረድ ጀምረዋል ያለው የክልሉ መንግስት፥ የክልሉን ህዝብ የመቻቻልና የአብሮ መኖር እሴት፣ ታሪክና ባህል በመጣስ በዘርና በኃይማኖት በመከፋፈል አስነዋሪ እርምጃም በመውሰድ አገሪቱን የብጥብጥና የሁከት አውድማ ለማድረግ በሙሉ አቅማቸው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብሏል።
በዚህም በምዕራብ ጉጂ፣ በምእራብ ሸዋ፣ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች ጥቂት ወረዳዎችና ከተሞች መንግስታዊ ድርጅቶችን፣ የኢንቨስትመንት ተቋማትን፣ መሰረተ ልማቶችንና የግለሰቦች ንብረቶችን አውድመዋል ነው ያለው።
በእነዚሁ አካባቢዎችም ህዝባዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ማድረጋቸውን አንስቷል።
እነዚህ ኃይሎች ጥፋት እያደረሱ ያሉት በትጥቅ በመታገዝ እና የሽብርተኛ ድርጅት አርማን በግልጽ አንግበው በመሆኑ የሀገሪቱ ህዝቦች የተቀዳጇቸውን ድሎች ለመቀልበስ እንዳለሙ ያሳያልም ነው ያለው መግለጫው።
በመሆኑም መላው የክልሉ ህዝብ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሲቪክ ተቋማት ከመንግስት ጎን በመቆም የሰላም ማስከበር ድርሻቸውን እንዲወጡ የክልሉ መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።
መንግስት የህግ የበላይነትና የህዝብን ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ግዴታውን ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አመላክቷል።