አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት ለያዛቸው እቅዶች ስኬት የሚጥር ለህዝብ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አዲስ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ገለፀ።
የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት፥ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የካቢኔ አባላትን መርጠው ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ።
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ቀደም ሲል በምክር ቤቱ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ ተመስርቶም፥ ከአባላቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት አቶ ጌታቸው።
የመልካም አስተዳደርና የልማት ተደራሽነት ችግሮችን ለመፍታት በተያዘው ዓመት የሚሰሩ ስራዎችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል።
የካቢኔ አባላት ምርጫ አቅምን፣ ቁርጠኝነትንና ውጤታማነትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፥ የካቢኔ አባላቱ የሃገሪቷን ህግና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡና በትጋት የሚሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
በገዥው ፓርቲ ትልቅ ሃላፊነት ላይ ያልነበሩ ግለሰቦችም አዲስ በሚዋቀረው ካቢኔ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፥ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ ሙሉ ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱ፣ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ፣ በህዝብ ተጠቃሚነትና ይህንን ለማረጋገጥ በተቀረፁ ፖሊሲዎች አፈፃፀም ላይ ሙሉ እምነት ያላቸው አባላትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያካትታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ በሚዋቀረው ካቢኔ ከነበሩበት ሃላፊነት ተነስተው ያላቸውን አቅምና ቁርጠኝነት መሰረት አድርጎ የተሻለ ሊፈፅሙ ወደ ሚችሉበት የሃላፊነት ቦታ ሊዛወሩ የሚችሉ ይኖራሉም ብለዋል።
በክልሎች ደረጃ በኦሮሚያ የተደረገው አይነት ለውጥ በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
መንግስት የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስና የሃገሪቷን ፈጣን እድገት ለማስቀጠል እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት የህዝቡ ተሳትፎ ቀጣይነት እንዲኖረውም አቶ ጌታቸው አሳስበዋል።