አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ ማምሻውን አጠናቋል።
በማጠቃለያው የ2009 በጀት አመት የስራ እቅድ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የድህነት ቅነሳ፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በዘንድሮው በጀት አመት ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አንስቶ ተወያይቷል።
ምክር ቤቱ በበጀት አመቱ የ11 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እቅድ ማስቀመጡንም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ገልጸዋል።
ለእቅዱ ስኬትም አመራሩ በንቃት ህብረተሰቡን ማገልገል እንዳለበት አቶ አባይ ተናግረዋል።
አቶ አባይ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍም ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችን የመገምገም እና የማጥራት ስራ በቀጣይ ሳምንታት ይካሄዳልም ነው ያሉት።
እድገቱን ለማረጋገጥም፥ በገጠር ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን በስፋት ማምረትና በከተማ ስራ አጥነትን በመቅረፍ ከተሞችን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአፈጻጸም ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላትም፥ በየደረጃው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ሶስት ረቂቅ አዋጆች ቀርበውም በሙሉ ድምጽ ፀድቀዋል።
የጸደቁት የገቢ ግብር አዋጅ፣ የግብር አስተዳደር አዋጅ ሲሆኑ፤ ለክልሉ እንዲቀርብ የተጠየቀው ተጨማሪ የ1 ነጥብ 49 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀትም በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።