አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የስንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከበር የሃገራችን ብሔራዊ ጥቅም ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት የተሳተፉ አካላትን በመታገልና ለህግ አሳልፎ በመስጠት መሆን እንዳለበት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚከበርውን የስንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከታሪካችን የነፃነታችን አርማ፤ ከብዝሃነታችን በመፈቃቀድ ላይ ለመሰረትነው የዲሞክራሲ አንድነታችን ስንደቅ ዓላማችን መገለጫ በመሆኑ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ለሃገሩ ስላም ርብርብ እንዲያድርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ስንደቅ ዓላማችን በዓለም ላይ ከፍታው እየጨመረ መጥቷል ያሉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፥ ይህም የኢትዮጵያ ህዝቦች በድህነት ላይ የከፈቱት ዘመቻ ውጤት በማስመዝገቡ የተገኘ እንደሆነም አብራርተዋል።
በድህነት ላይ የሚደረግ ትግል ተጠናክሮ በመቀጠሉ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለመቀልበስ የሃገራችን ብሔራዊ ጥቅም ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት የተሰለፉትን ፀረ ስላም ሀይሎች መታገልም ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ስንደቅ ዓላማችን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሃገሪቱ ተግባራዊ እያደረገች ነው።
የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ሰራ መጀመሩ በመንግስትና በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ የፈጠር መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ሙላቱ፥ የሰንደቅ ዓላማ ትርጉም ጥልቀት የሚኖረው በየደረጃው ህብረተስቡ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ሲሆን በመሆኑ ይህ የተሳካ እንዲሆንም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የተመጀረውና የተመዘገበው ልማት በሃገሪቱ ቀጣይነት የሚኖረው ሰላም ሲሰፍን ነው፤ የሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የሃገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ አልፎ የሌሎች ሃገሮችን ሰላም በማስጠበቅ የላቀ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር እያደረገ ላለው አስተዋፅኦ ያላቸውን አድናቆት የገለፁት ፕሬዝዳንት ሙላቱ፥ መላው ህዝብ በልማት አርብኝነት ለሃገሩ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነት መገለጫ፣ በብዝኃነት ላይ የተመሰረተ አንድነታችን አርማ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
በሰንደቅ ዓላማ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 863/2006 መሰረት ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር የመጀመሪያው ሰኞ እንዲከበር ተደንግጓል።