አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰበታ ከተማ ተከስቶ በነበረው ሁከት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ሶስት ፋብሪካዎች ውጪ ሌሎቹ አስፈላጊው ጥበቃ ተደርጎላቸው ወደ ስራ መመለሳቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማዋ አስተዳደር ዛሬ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የከተማዋ ከንቲባ አቶ አራርሳ መርደሳ እንደተናገሩት፥ ከጉዳቱ ጋር ተያይዞ የጥበቃና የሚያስፈልጉ ጊዜያዊ ድጋፎች በማድረግ ከሶስት ፋብሪካ ውጪ የቀሩት ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።
አሁን ስራ ያልጀመሩት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ፋብሪካዎችም በቅርቡ ወደ ስራ የሚገቡበት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አከባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ከፍተኛ የንብረት ጉዳትን ያስተናገደችው ሰበታ ከተማ ነበረች።
በነውጥ አዘሉ ሁከት 11 ፋብሪካዎች እና 62 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።
የተቃጠሉት ፋብሪካዎች ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ነበሩ።
ይህን መነሻ ያደረገው የሰበታ ከተማ ባለሀብቶች የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ ሲካሄድ፥ መሰል ሁከት እና ግርግር ዳግም እንዳይከሰት የከተማ አስተዳደሩ እና ባለሃብቶች በጋራ መስራት ባለባቸው ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የሰላም ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች የሰበታ ከተማ ከንቲባ ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ አራርሳ መርዳሳ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ውይይት የጥፋት ሀይሎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባና ህብረተሰቡን የማይወክሉ እንደሆኑ ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
ይህን ተከትሎ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ማጣራት እስካሁን 1 ሺህ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ያሉት ከንቲባው፥ ከእነዚህ ውስጥ የከተማዋ ነዋሪዎች ከ50 እንደማይበልጡ ተናግረዋል።
ንብረት ባወደመው ሁከት ከተሳተፉት አካላት ሰፊውን ድርሻ የሚይዙት ልዩ አላማ ያላቸው አካላት እንደሆኑ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባልም ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት ባለሀብቶች ግን በእለቱ የነበረው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በአግባቡ ሊጤን ይገባል ብለዋል።
ከጸጥታ ሀይሉ እና የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ጋር ተያይዞ መፋዘዞች ነበሩ በሚል ከባለሀብቶች ለተነሱት ጥያቄዎች አስተዳደሩ ጥልቅ ምርመራ እና ማጣራት እያካሄደ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል አቶ አራርሳ።
በሰላም ኮንፈረንሱ ተመሳሳይ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ተደርጓል።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በቀጣይ ፋብሪካዎችን እና የኢንቨስትመንት ተቋማትን በተለየ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል ስርአት እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።