Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጎብኚዎች ተዘዋውረው ለመጎብኘት ማንንም ማሳወቅ እንደማይጠበቅባቸው የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገለጸ

visitors
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ለመጎብኘት ማንንም ማሳወቅ እንደማይጠበቅባቸው የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ ከ40 ኪሎ ሜትር ክልል በላይ ሳያሳውቁ እንዳይንቀሳቀሱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገጉ የሚታወስ ነው።
አዋጁ ሃገርንና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን የሚመለከት እንዳልሆነ ነው የተገለጸው።
ዋና ዓቃቤ ሕግ ጌታቸው አምባዬ እንዳሉት፥ ጎብኚዎችን በተመለከተ የሚደረገው እንቅስቃሴ ወትሮ ከሚደረገው እንቅስቃሴ የተለየ አይሆንም።
ማንኛውም የጎብኚ ቪዛ ይዞ የሚመጣና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመጎብኘትና ሌሎች ሥራዎችን ለመስራት የሚፈልግ፥ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ማሳወቅ እንደማያስፈልገውም ተናግረዋል።
ማንኛውም ሃገር ጎብኚ ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ እንደሚችል የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፥ ጎብኚዎች ወደ ሃገሪቱ ሲመጡ ከዚህ ቀደም በተለመደው የአሰራር ሥርዓት እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው በበኩላቸው፥ ጎብኚዎች በሠላሙ ጊዜ በቡድንም ሆነ በግል ይንቀሳቀሱ እንደነበር ሁሉ አሁንም በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው መጎብኘት ይችላሉ ብለዋል።
በመሆኑም አዋጁ ቱሪስቶች የሃገሪቱን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት የያዙትን እቅድ እንዳይሰርዙና ምቾት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ ወደ ተረጋጋ ሠላሟ እየተመለሰች በመሆኑ ጉብኝታቸውን የሚሰርዙ ጎብኚዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱንም ገልጸዋል።