Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጫማዎችን መረከብ ትጀምራለች

evanca-trupm
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዳሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሂላሪ ክሊንተን ጋር የሚፎካከሩት ዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ከቻይና ኩባንያዎች ጫማዎችን ትረከባለች።
በቅርቡ ግን ከቻይና ሳይሆን ከኢትዮጵያ ጫማዎችን መረከብ እንደምትጀምር ተገልጿል።
በቻይና በኢቫንካ ትራምፕ ስም ጫማዎችን የሚያመርተው የሁጂያን ግሩፕ ሀላፊ ዣንግ ሃውሮንግ፥ በዚህ ሳምንት የኩባንያውን ምርት ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ለማዘዋወር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ዣንግ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጹት፥ በኢቫንካ ትራምፕ ብራንድ የሚመረቱን ጫማዎች በኢትዮጵያ ለማምረት የታቀደው በሀገሪቱ ሰፊ እና ርካሽ የሰው ሀይል በመኖሩ ነው።
ሁጂያን ግሩፕ በአዲስ አበባ የማምረቻ ህንፃዎች፣ የሰራተኛ መኖሪያ ቤቶች እና ሆስፒታል ያካተተ “ቀላል የኢንዱስትሪ ከተማ” በአዲስ እየገነባ መሆኑን አስታውቋል።
ሁጂያን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ለ30 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የመፍጠር ግብ እንዳለውም ነው ሀላፊው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራቾችን ቀልብ መሳብ ከጀመረች ሰነባብታለች።
እንደ ኤች ኤንድ ኤም፣ የአሜሪካው ፒ ቪ ኤች ፣ የህንዶቹ አርቪንድ እና ሬይሞንድ ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ልማት ላይ ተሰማርተዋል።
መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየገነባቸው የሚገኙ የኢንዱስትሪ ዞኖች እና አነስተኛ የምርት ወጪ ሀገሪቱን ተመራጭ እያደረጓት ነው።
አሜሪካ የሰጠችው እና ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የሆነችበት የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ እና ኮታ ነፃ ወደ አገሯ እንዲያስገቡ የሰጠችውን እድል /አጎዋ/ የመሰሉ ስምምነቶች የኢትዮጵያ ምርቶች ከቀረጥ እና ኮታ ነፃ ወደዚህች አገር ገበያ እንዲገቡ አስችሏል።
ይህም በተለይም በጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ ልማት ዘርፍ ተሰማርተው ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ እየላኩ ያሉ የውጭ አገራት ኩባንያዎችን ተጠቃሚ አድርጓል።