700 ሺሕ ዶላር መድቦ ጥናት እያካሄደ ነው
የዓለም ባንክ የአዲስ አበባ ከተማ ምጣኔ ሀብት የሚያድግበትንና የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሻሻልበትን ሁኔታ በሚመለከት እያካሄደው ባለው ጥናት፣ የመጀመሪያውና ዋና እንቅፋት ሆኖ ያገኘው የመሬት አቅርቦትና የመሠረተ ልማቶች አለመሟላት መሆኑን አስታወቀ፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ የዓለም ባንክ የከተማ ልማት ከፍተኛ ባለሙያና ባንኩ ትኩረት ባደረገባቸው አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ የአራት አፍሪካ አገሮች የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል የፕሮጀክት አስተባባሪ ሚስ ኢማ ሆብሰን፣ ከአስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ጥቅምት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ስለማሻሻል፣ የከተማውን ኢኮኖሚ ዕድገት እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻልና ሌሎች ችግሮችን በሚመለከት እያደረጉት ስለሚገኘው ጥናት የመጀመሪያ ምዕራፍ ክንውን ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸውን ጨምሮ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ ሚስ ሆብሰን እንደተናገሩት፣ በተለይ በግል ዘርፉ የሚታዩ ችግሮች በርካታ ቢሆኑም የሥራ ፈቃድና መሬት አለማግኘት፣ የመሠረተ ልማቶች አለመሟላት ተቀዳሚ ችግሮች ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ አልሚዎችን በፋይናንስም ሆነ አቅማቸውን ማሳደግ በሚገባ መርዳት ተገቢ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ያን የዘነጋው እንደሚመስል ተናግረዋል፡፡
የዓለም ባንክ በተለይ የግሉ ዘርፍ እንዴት ማደግ እንዳለበት፣ እስካሁን የተፈለገውን ያህል ዕድገት ላያመጣ የቻለው ለምን እንደሆነና በቀጣይ የከተማ አስተዳደሩ ዕርዳታ ታክሎበት እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል፣ ለሁለት ዓመታት ጥናት ለማድርግ 700 ሺሕ ዶላር በጀት መድቦ እየሠራ እንደሚገኝ ሚስ ሆብሰን አስረድተዋል፡፡ ኢንቨስተሮች ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻቸው ጉዳዮቻቸው በፍጥነት እንደማይፈጸሙላቸውና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው፣ ባደረጉላቸው ቃለ ምልልሶች ማረጋገጣቸውን ለውይይቱ ተካፋዮች አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አሁን ያለችበት የዕድገት ሁኔታ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ የቻይናዋ ጉዋንግዡ ከተማና የብራዚሏ ሳኦፖሎ ከተማ የነበሩበት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆሙት ሚስ ሆብሰን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማመቻቸትና የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በማስቀጠል፣ በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መድረስ እንደምትችል አመልክተዋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ አቅምን በማሳደግና ከሌሎች አገሮች የተገኙ ልምዶችን ተግባራዊ በማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ለግሉ ዘርፍ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች በሌሎቹም የአፍሪካ አገሮች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ጠቁመው የመሬት አቅርቦት ችግር፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሥርዓት ችግር፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችና የቀጣሪዎች የዕውቀት ማነስ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን፣ እነዚህ ከተፈቱ ግን ልማትን ማስቀጠልና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ የዓለም ባንክ በጥናቱ ያገኛቸው ችግሮችና የሚፈቱበትን መንገዶች በጥናቱ መጨረሻ ካረጋገጠ በኋላ፣ ከከተሞቹ ጋር አብሮ የሚሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አገር በኢኮኖሚ ዕድገቷ ላይ ጥሩ ብትሆንም በሥራ ፈጠራ ላይ ግን ብዙ መሥራት እንዳለባት የጠቆሙት ሚስ ሆብሰን፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋትና በመደገፍ የሥራ ዕድል መክፈት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ የንግድ ተቋማት፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲያመርቱ መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡
ጥናታቸውን ባለማጠናቀቃቸው ሁሉንም ደምድመው መናገር እንደሚቸግራቸው የገለጹት ሚስ ሆብሰን፣ በመጀመሪያ ጥናታቸው ላይ ያረጋገጧቸውን የኢንቨስትመንት እንቅፋቶች የአስተዳደሩ ሁሉም ኃላፊዎች በደንብ እንደሚያውቋቸው ተናግረዋል፡፡ ከኢንቨስተሮች ለሚነሳ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ትልቁ ችግር የፋይናንስ እጥረት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ራሳቸውን አሻሽለው አቅም በመገንባት አሠራሮችን በማሻሻል ሥራዎችን ማከናወን እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
የዓለም ባንክ ተወካይ በመጀመሪያ ደረጃ ጥናታቸው ያረጋገጧቸውን ችግሮችና ጥሩ ተሞክሮዎች አስተዳደሩም በደንብ አውቋቸው እየሠራ በመሆኑ፣ ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉ መሆኑን አቶ አሰግድ ገልጸዋል፡፡
የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳለውና ከፍተኛ ዕርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ አሰግድ፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢኮኖሚ ዕድገቱን እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል የሚያደርገው ጥናት ሲጠናቀቅ፣ ጠቃሚ ነገሮች ሊገኙ እንደሚችሉ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ ሲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት፣ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ አንድ ላይ በመሆን ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አቶ አሰግድ ተናግረዋል፡፡ አገሪቷም ሆነች ከተማው የፖሊሲ ችግር እንደሌለባቸው የገለጹት አቶ አሰግድ፣ በጥናቱም እየታየ ያለው አስቀድሞ አስተዳደሩ የሚያውቃቸው የአተገባበር ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በቂ ዕውቀት አለመኖርና የአቅም ማነስ በዋናነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ በስፋት እየሠራበት መሆኑንም አክለዋል፡፡ በቅርቡ የተጀመረውን የከተሞች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮጀክትን በመጠቀም የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲኖር እየሠሩ መሆናቸውን፣ ለአሥር ዓመታት የሚሆን ፍኖተ ካርታ ተቀርፆ በአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር የዓለም ባንክና ኢትዮጵያ በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዓለም ባንክ በጥናቱ እንዳረጋገጠው የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የመሬት አቅርቦት፣ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩላቸው መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ከተማው እየሠራው የሚገኘው የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ መመዘኛ (Doing Business) ፕሮጀክት ላይ ያለባቸው ችግር በከተማው ድረ ገጽ አዳዲስ መረጃዎችን አለማስቀመጥ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አሰግድ፣ በተለያዩ አገሮች ያሉ ኢንቨስተሮች የሚያስፈልጉዋቸውን መሥፈርቶች በቅድሚያ አሟልተው እንዳይቀርቡ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ ችግሩን ተረድቶ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር አዲስ ሶፍትዌር የማበልፀግ ሥራ ተሠርቶ ስለተጠናቀቀ፣ ሁሉም የከተማው መረጃ በቅርቡ እንደሚቀመጥ አቶ አሰግድ አስታውቀዋል፡፡