አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን አባል በመሆንና ከታጣቂዎች የክላሽ መሳሪያ በሃይል በመቀማት ሁከት ለመፍጠር ሲቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰባት ግለሰቦች ላይ ክሰ ተመሰረተ።
በዛሬው እለት ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች 1ኛ ተስፋዬ ጉታ ቱምሳ በቅጽል ስሙ አብዲ ጉታ፣ 2ኛ ሲሳይ ገበየሁ ሽፈራሁ፣ 3ኛ መገርሳ ድሮን ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች ናቸው የሸብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሴር እና በማነሳሳት ክስ የተመሰረተባቸው።
የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ ራሱን የኦነግ አባል በመሆን ከውጪ ሃገር ከሚገኘው የሸብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፈጠር የሃገሪቱን ህገ መንግስታዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቁማትን ለመናድና ለማፈራረስ የሽብር ተልዕኮ በመቀበል በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች አባላትን በመመልመልና ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት አደራጅተዋል።
1ኛ ተከሳሽ በኢሜይል አድራሻው ተጠቀሞ ከሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ለሁከት ለብጥበጥ ወጣቶችን ማደራጀታቸውን፣ በአካባቢው ያሉ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማደረግ ቃል መግባታቸውን፣ ዘመናዊ መሳሪያ አጠቃቀም ስልጠና ለአባላቱ መሰጠቱንና ቡድኑም የወታደራዊ ትጠቅ ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቁም በክሱ ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ የሀሰት የፌስቡከ አድራሻ በመክፈት የሸብር ቡድኑ አባል ከሆኑ ሶስት ግለሰቦች ጋር የኦነግን አላማ እንዴት ማሳካት እንዳለባቸው፣ በምእራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ብጥብጠና ሁከት እንዲያነሱ እና ሁከቱን መመራት እንዳለባቸው መረጃ መለዋወጡንም ክሱ ያስረዳል።
ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያሉ ተከሳሾች ግንቦት 29 2008 ዓ.ም በዞኑ አፋና ጮቢ በተባለ አካባቢ ከታጣቂ ሚኒሻ የጸጥታ ሃይል የክላሽ መሳሪያ ከ20 ጥይት ጋር በሃይል ቀምተው ጫካ ገብተዋል ነው የሚለው ክሱ።
6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ደግሞ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ቀበሌ 04 ፉሪ በተባለ አካባቢ ጫካ በመግባት መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለማፈራረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ በከተማዋ ውሰጥ የጸጥታ ሃይል ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ መረጃ ማቀበላቸው ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ከታጣቂዎች መሳሪያ በመቀማት፣ ከሽብር ቡድኑ አመራሮች መረጃ በመቀበል፣ በሴል በመደራጀትና ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ፣ ጥቃት ለማድረስ አስፈላጊውን መረጃ በመቀበልና ትዕዛዝ በመስጠት በአንድ ላይ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በዚህም መሰረት ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሸብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሴር እና በማነሳሳት ክስ መስርቶባቸዋል።
ከሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት የክስ ዝርዝር ለተከሳሾቹ እንዲደርስ አድርጓል።
ተከሳሾቹ ከጠበቃ ጋር ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።