Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ 6ኛ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

morocco-president
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ 6ኛ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሩዋንዳ አቀኑ።

አንድ የሞሮኮ ንጉሥ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገራት ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግ ንጉሥ መሐመድ 6ኛ የመጀመሪያው ናቸው።

ንጉሥ መሐመድ ከኢትዮጵያና ሩዋንዳ ባሻገር ታንዛኒያን የሚጎበኙ ይሆናል።

ሞሮኮ ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ የሚባል ባለመሆኑ የንጉሡ ጉብኝት ግንኙነቱን ማጎልበትን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።

አገሪቷ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1984 ራሷን ከአፍሪካ ህብረት በይፏ ማግለሏ የሚታወስ ነው።

የማግለሏ ምክንያት ደግሞ የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሞሮኮ “ግዛቴ” የምትላትን ሰሃራዊ ዴሞክራቲክ ዓረብ ሪፐብሊክን በአባልነት መቀበሉ ነው።

ይህን ተከትሎ ሞሮኮ የአፍሪካ ህብረት አባል ያልሆነች ብቸኛ አገር ሆና ለ30 ዓመታት ቆይታለች።

ባለፈው ሐምሌ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ግን ሞሮኮ ዳግም ወደ አፍሪካ ህብረት ለመመለስ ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።

ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ሞሮኮ እንደ ግዛቷ ለምትቆጥራት ሰሃራዊ ዴሞክራቲክ ዓረብ ሪፐብሊክ ዕውቅና በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩ አገራት ናቸው።

እናም የንጉሡ ጉብኝት እነዚህ አገራት ከሰሃራዊ ዓረብ ሪፓብሊክ ጋር የጀመሩትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም እንዲያጤኑት ለመነጋገር እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል።

ንጉሥ መሐመድ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ባለፈ ከአገራቱ ጋር በኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ዙሪያ እንደሚመክሩ የሚጠበቅ ሲሆን የአገሪቷ ዕውቅ የቢዝነስ ሰዎችና ኩባንያዎችም በጉብኝቱ መካተታቸውን የመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሞሮኮ የአገር ውስጥ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የኢንዶውመንትና የእስልምና ጉዳዮች፣ የኢኮኖሚና ፋይናንስ፣ እንዲሁም የግብርናና የዓሳ ኃብት ሚኒስትሮች በንጉሡ ጉብኝት የተካተቱ ናቸው።

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ ባለፈው ሰኔ ሞሮኮን ለሦስት ቀናት የጎበኙ ሲሆን ይህን ተከትሎም ሞሮኮ በዚህ ዓመት መጨረሻ ኤምባሲዋን በሩዋንዳ እንደምትከፍት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሳላሃዲን ሜዝዋር ይፋ አድርገዋል።