Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የህዳሴ ግድብ 54 በመቶ ተጠናቀቀ ሲባል ምን ማለት ነው…?


አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰሞኑን ታላቁ የህዳሴ ግድብ 54 መቶ መድረሱን የሚያመላክቱ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል።
መንግስትም በፕሮጀክቱ ንድፍ መሰረት የግድቡ ሙሉ በመሉ መጠናቀቅ ሳይጠበቅ በቅርቡ እስከ 750 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል ለማመንጨት ዝግጅት መደረጉን ገልፅዋል።
ግድቡ 54 በመቶ ተጠናቀቀ ሲባል ምን ማለት ነው? ከሌሎች ሀገራት ግድቦች ተሞክሮ አንፃር ከግደቡ ግንባታ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት እቅዱ የመሳካት እድል ምን ያህል ነው?
የኤም ኤች ኢንጅነሪንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢንጂነር መሰለ ሃይሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የግድቡ ግንባታ 54 በመቶ ተጠናቀቀ ሲባል የመቶኛ መለኪያው በአብዛኛው ፕሮጀክቱ ወጪ ላይ ያተኮረ ነው ይላሉ።
“የግድቡን ግንባታ እንደ ባለሙያ ስመለከተው፤ የግድብ ስራ ውሃውን አቅጣጫ ማስቀየር እና የቆፋሮ ስራ በጣም አድካሚው ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ሆኖም ግን ስራው በገንዘብ ሲለካ አፈር ማንሳት ስለሆነ ብዙ ገንዘብ ስለማይጠይቅ ብዙ መስሎ አይታይም ብለዋል።
የግንባታ ደረጃ ብቻውን ቢለካ የመቶኛ ቁጥሩ ከ54 በመቶ ክፍ ሊል እንደሚችልም ዶክተር ኢንጂነር መሰለ ያብራራሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዋናው ግድብ 10 ነጠብ 1 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር የአርማታ ሙሊት የሚያስፈልገው ሲሆን፥ ከዚህ ወስጥ 7 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር አርማታው ተሞልቷል፤ ግድቡን በአርማታ ሞልቶ ለማጠናቀቅ የሚቀረው ስራ 3 ሚልየን ኪዩቢክ ሜትር አርማታ መሙላት ነው።
ዶክተር መሰለ፥ በእስካሁኑ የግንባታ ሂደት የገንዘብ ወጪው ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት በመቶኛ ሲገለፅ መጠኑ ዝቅ ቢልም የግድቡ ፈታኝ የሚባሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ አካል የሆኑ፣ ከባድ እና ውስብሰብ ጊዜን የሚጠይቁ ዋና ዋና ስራዎችም መታለፋቸውን ያነሳሉ።
ዶክተር ኢንጂነር መሰለ የአባይ ውሃን አቅጣጫን ከማስቀየር ጀምሮ ወደ ተፈጥሯዊ መፍሰሻ ስፍራው እስከ መመለስ፤ ይህን ተከትሎም ውሃው የሚያልፍበት የግድቡን አካል፣ ቀድሞ ውሃው በሚያልፍበት ስፍራ እስከ መገንባት ድረስ ከባድ እና ውስብስ የሚባሉ ስራዎች ባለፉት አመታተ ተከናውነዋል።
ይህም ከፈታኝ ስራዎቹ ሁሉ ዋናው ነበር ይላሉ።
አሁን እነዚህ ስራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን፥ ግድቡም ከመሬት ከፍ ብሎ የዋናው ግድብ ቁመት ባለፈው አመት 70 ሜትር ደርሶ ነበር፤ አሁን መጠኑ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ዶክተር መሰለ እንደተናገሩት፥ በመቶኛ ሲገለፅ ያነሰ መስሎ የሚያታየው የእስካሁን ፕሮጀረክቱ አፈፃፀም ቴክኒካዊ በሆነ እይታ ሲቃኝ ግን የግድቡ ግንባታ ደረጃ በመቶኛ ከተገለፀው በላይ ነው።
የፕሮጀክቱ አካል የሆነ ግን በመቶኛ አፈፃፀሙ ያልተዳሰሰ ስራም አለ፣ ይህም ከግድቡ ሰፍራ ወደ በለስ እና ወደ አዲስ አበባ የተዘረጉት ባለ 400 እና 500 ኪሎ ቮልት የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ናቸው።
እነዚህ መስመሮች ዝርጋታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ መስመሮቹ ግድቡ ሃይል ማመንጨት ሲጀመር ወደ ብሄራዊ የሃይል ቋቱ የኤሌክትርክ ሃይል በቀጥታ እንዲልክ የሚያስችሉ ናቸው።