Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከታጣቂ ሚሊሻዎች ጠብመንጃ በመንጠቅ ለሽብር ተግባር ተሰማርተዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

olf-court-apparance
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ውስጥ ከታጣቂ ሚሊሻዎች ላይ ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃ በመንጠቅ ወደ ጫካ በመግባት፣ በሽብር ተግባር ተሰማርተው ነበር ባላቸው ሰባት ግለሰቦች ላይ ክስ መሠረተ፡፡
ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው በቅጽል ስሙ አብዲ ጉታ የሚባለው ተስፋዬ ጉታ ኩምሳ፣ ሲሳይ ገበየሁና መገርሳ ዲሮን ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች የአካባቢውን ፀጥታ ከሚያስጠብቁ ታጣቂዎች ላይ ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃ በመንጠቅ ሁከት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ተከሳሾቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል መሆናቸውንና በውጭ አገር ከሚገኙ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ክሱ ይገልጻል፡፡
የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማፈራረስ የኦነግን ተልዕኮ በመቀበል በተለይ በምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች አባላትን በመመልመልና ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት ሲያደራጁ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ተስፋዬ የተባለው ተከሳሽ ከኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኢሜይል በመገናኘት፣ ወጣቶችን ለሁከትና ብጥብጥ ለማደራጀት የአካባቢው ባለሀብቶች ድጋፍ ለማድረግ እንዲስማሙ ሲነጋገር እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ፣ ተከሳሹም ወጣቶቹን በማሰባሰብ የዘመናዊ መሣሪያ አጠቃቀም ሥልጠና መስጠቱንና የወታደራዊ ትጥቅ ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቁን አክሏል፡፡
ተከሳሾቹ ሐሰተኛ የፌስቡክ አድራሻ በመክፈትና የኦነግን ዓላማ እንዴት ማሳካት እንዳለባቸው ከአመራሮቹ ጋር በመመካከር፣ በምዕራብ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ ብጥብጥና ሁከት እንዴት እንደሚያስነሱና ብጥብጥና ሁከቱን እንዴት መምራት እንዳለባቸው መረጃ ሲለዋወጡ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
በምዕራብ ሸዋ አፋና ጮቢ በተባለ አካባቢ ከታጣቂ ሚሊሻ የፀጥታ ኃይል ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃ ከነጥይቱ ነጥቀው ጫካ መግባታቸውን፣ መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለኦነግ አመራሮች መረጃ ሲያቀብሉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
ተከሳሾቹ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁር 652/2001 አንቀጽ 4 ማለትም የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን በመግለጽ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ተከሳሾች ክሱ ተሰጥቷቸው መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter