Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኢህአዴግ ያካሄደውን ግምገማ መሠረት በማድረግ በፌዴራልና በክልል የአመራር ምደባን በውጤታማነት ላይ ተመስርቶ እንደሚያስተካክል ገለፀ

ethioeprdf
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ/ ያካሄደውን ግምገማ መሠረት በማድረግ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግስት የአመራር ምደባ በውጤታማነት ላይ ተመስርቶ ማስተካከያ እንደሚደረግ አስታወቀ።

የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከጥቅምት 14 እስከ 17 ቀን 2009 ድረስ ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላው መግለጫ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው በውጤታማት መቀጠሉን ነው ያስታወቀው።

በተለይም ከሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የቀረቡት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ሪፖርቶችን ተመልክቶ ሂደቱ በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት እየሄደ መሆኑን እንዳረጋገጠ አመልክቷል።

ኢህአዴግና አባል ብሄራዊ ድርጅቶቹ የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ የሆኑትን ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል ያለው መግለጫው፥ በአገሪቱ ለሩብ ምዕተ አመት የዘለቀው ፈጣን እድገት ቀደም ሲል ለዘመናት አገሪቱ የተጓዘችበትን የማሽቆልቆል ጉዞ በአስተማማኝ ደረጃ ቀልብሶ ወደፊት እንድትራመድ አስችሏል ብሏል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፉት የተሃድሶ አመታት በአገሪቱ የተመዘገቡ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ድሎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአመራር የአሰራር ጉድለቶች ምክንያት የታዩ ችግሮች ስርዓቱ ለአደጋ መጋለጥ ጀምሮ እንደነበር በግምገማው ማረጋገጡን ነው ያመለከተው።

በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው ወቅታዊና መሰረታዊ ሆኖ የተከሰተበት አይነተኛ ምክንያትም ይኽው ነበር ብሏል።

በቅርቡ ለተከሰቱት የሰላምና መረጋጋት ችግሮችና ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ጉዳቶች መንስኤ የሆነውን ጉድለት መሰረት በማድረግ ከኢህአዴግና ከብሄራዊ ድርጅቶቹ ከፍተኛ አመራሮች ጉድለቶች ግምገማ በመጀመር በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች ትክክለኛ ፈር ይዞ መቀጠሉን አረጋግጧል።

ኢህአዴግ የታዩት ጉድለቶች ምንጫቸው የህብረተሰባዊ ለውጥ ማምጫ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግለው የመንግስት ስልጣን ወደ ግል ኑሮ ማሻሻያነት ጥቅም በመዋሉ እንደሆነ በየብሄራዊ ድርጅቶቹ በተደረጉ ግምገማዎች በድጋሚ አረጋግጫለሁ ብሏል።

ዛሬም ከመጣው ለውጥ በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የወጣቱ ህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጉድለት እንዲስተካከልላቸው የሚሹና የሚጠይቁ መሆኑን በአፅንኦት በመገንዘብ እነዚህን ህዝባዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ለመመለስ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን መግለጫው ጠቁሟል።

የጉድለቶች ምንጭ የመንግስትን ስልጣን ለህብረተሰባዊ ለውጥና ለህዝቡ ቅንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከመጠቀም ይልቅ ለግል ኑሮ መጠቀሚያ ማድረግ ነው ያለው መግለጫው፥ ይህንኑ ለማስተካከል በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን ማጎልበትና ዳር ማድረስ እንደሚገባ ታምኖበታል ብሏል።

በመሆኑም ብሄራዊ ድርጅቶች በከፍተኛ አመራር ደረጃ የጀመሩት ራስን የማጥራት እንቅስቃሴ በየደረጃው ባሉ አመራሮች፣ በአባላትና በህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ነው ያለው።

ግምገማውን መሰረት በማድረግ የሰው ሀይል ምደባ ማስተካከያዎች እንዲደረጉና በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግስት የአመራር ምደባ በውጤታማነት ላይ ተመስርቶ ማስተካከያ በማድረግ አመታዊ ስራው በተጠናከረ አቅጣጫ እንዲፈፀም ለማድረግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።

የድርጅቱ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣም ህዝቡ የተለመደ ገንቢ ሚናውን በመጫወት የለውጡን ሂደት የማይቀለበስ ደረጃ ላይ እንዲያደርስም ጥሪ አቅርቧል።