Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በኦሮሚያ ክልል ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ኢንቨስተሮች የካሳ ጥያቄ እያቀረቡ ነው

sebeta-back-to-business
በመስከረም ወር መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ሁከት ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ኢንቨስተሮች፣ መንግሥት የተለያዩ ማካካሻዎች እንዲሰጣቸው መጠየቅ ጀመሩ፡፡
መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሳይከበር በቀረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ባለፈ ማግሥት፣ በኦሮሚያ ክልል ባገረሸው ተቃውሞ በርካታ ኢንቨስትመንቶች መውደማቸው ይታወሳል፡፡
ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ኢንቨስተሮች መንግሥት ማካካሻ እንዲሰጣቸው፣ ምክክር የሚደረግባቸው መድረኮችንም እንዲያዘጋጅ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡
በወቅቱ በተነሳው ሁከት ንብረት የወደመባቸውና የተለያዩ የማካካሻ ፓኬጆች እንዲዘጋጁላቸው ከጠየቁት መካከል የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ንብረት የሆነው ደርባ ሚድሮክ፣ የናይጄሪያው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶና አገር በቀሉ የውኃ ታንከር ፋብሪካ ሱፐር ፋይቨር ኩባንያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከሱሉልታ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ከሚገኘው ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሚንቶ የማጓጓዝ ሥራ የሚያከናውነው እህት ኩባንያ ደርባ ትራንስፖርት መሰንበቻውን በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበረው ሁከት፣ 54 ከባድ ተሽከርካሪዎቹ ከፍተኛና መካከለኛ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡
የደርባ ሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደርባ ሚድሮክ ከደረሰበት ውድመት በኋላ ያሉትን ከባድ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ወደ አዲስ አበባ ሰብስቧል፡፡ ውድመት ከደረሰባቸው 54 ተሽከርካሪዎች ውስጥ መሰባበር ያጋጠማቸውን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባትም እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል፡፡
‹‹ደርባ ሚድሮክ ለጠፋበት ንብረት መንግሥት የገንዘብ ካሳ እንዲሰጠው አይፈልግም፤›› ያሉት አቶ ኃይሌ፣ ነገር ግን መንግሥት የታክስና የግብር ቅነሳ እንዲያደርግለት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ደርባ የደረሰበትን ውድመት ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ማስታወቁን አቶ ኃይሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሌላው የሰሞኑ ችግር ሰለባ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ነው፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ ወረዳ በሙገር ሸለቆ ውስጥ የተቋቋመው ዳንጎቴ ሲሚንቶ፣ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡
ይህ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ሁከት ቀደም ሲል 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሞበታል፡፡ በክልሉ ዳግም ባገረሸው ተቃውሞ አራት የጥሬ ዕቃ ማውጪያ ማሽነሪዎችና ሁለት ተሽከርካሪዎች ወድመውበታል፡፡
የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአንዱ ጥሬ ዕቃ ማሽን ዋጋ ከስምንት ሚሊዮን እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ግምት አለው፡፡
ዳንጎቴ ሲሚንቶ 443 ከባድ ተሽከርካሪዎች በቅርቡ ከውጭ አስመጥቶ ነበር፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ የገቡ ሲሆን፣ በድጋሚ 500 ከባድ ተሽከርካሪዎችን የማስገባት ዕቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡
ዳንጎቴ ሲሚንቶ ቀደም ሲል ለወደመበት 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መንግሥትን ካሳ አለመጠየቁ ታውቋል፡፡ አሁንም ካሳ የመጠየቅ ፍላጎት ባይኖረውም፣ ከቀረጥ ነፃ የመሳሰሉ ፓኬጆች ተጠቃሚ በመሆን የጠፋበትን ንብረት ማካካስ እንደሚፈልግ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ በተከሰተው ሁከት በተለይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት በተከሰተበት ሳምንት፣ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ብቻ 11 ፋብሪካዎችና 62 ከባድ የሕዝብና የጭነት ማመላለሻዎች ወድመዋል፡፡ ውድመት ከደረሰባቸው መካከል የውኃ ታንከር አምራቹ ሱፐር ቫይቨር ይገኝበታል፡፡
ሱፐር ቫይቨር ኩባንያ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎችና ያለቀላቸው ምርቶች  ተቃጥለዋል፡፡ የሱፐር ፋይቨር ኩባንያ ባለድርሻ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግሥት ጌትነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የወደመው ንብረት 35 ሚሊዮን ብር ይገመታል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት በመሆኑ ወደ ሥራ ተመልሰናል፡፡ ነገር ግን ያለን ጥሬ ዕቃ ውስን በመሆኑ ሥራችን ዘላቂ ላይሆን ይችላል፤›› በማለት የገለጹት ወይዘሮ ትዕግሥት፣ ‹‹መንግሥት ለወደመው ንብረት ካሳ እንዲከፍል ጥያቄ አቅርበናል፡፡ የፋብሪካውን ውድመት ለመጎብኘት ለመጡ ባለሥልጣናትም ይህንኑ ገልጸናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለወደሙ ንብረቶች መንግሥት ካሳ ለመክፈል የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከቀረቡለት 22 የካሳ ጥያቄዎች መካከል ሰባት ለሚሆኑት ካሳ ለመክፈል እየተዘጋጀ ነበር፡፡
ነገር ግን በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቀው የመስከረሙ የንብረት ውድመት ሌሎች ተጨማሪ የካሳና የማካካሻ ጥያቄዎች እንዲቀርቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ 
Source ; Reporter