አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰበታ ከተማ ህዝባዊ የሰላም ጉባዔ ዛሬ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ ላይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች ተከስቶ የነበረው ሁከት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴአቸው ላይ ተፅእኖ ፈጥሮባቸው እንዳለፈ ተናግረዋል።
በህዝባዊ ጉባኤው ላይ መሰል ሁከት እና ግርግር ዳግም እንዳይከሰት የከተማ አስተዳደሩ እና የከተማዋ ነዋሪዎች በጋራ መስራት ባለባቸው ጉዳይ ላይ ምክክር አድርገዋል።
በጉባኤው ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ የተለያዩ ምክክሮች በመደረግ ሲሆን፥ በዚህም ላይ በሰላማዊና ማህበራዊ ኑሮዋ የምትታወቅ በመሆኗ ስሟን ለማጠልሸትና ልዩ ፍላጎት ለማሳካት ተብሎ የተከሰተው ሁከት እንደነበር ተገልጿል።
ሁከት እና ግርግሩ ምንም አይነት ህዝባዊ መሰረት የሌለው እንደሆነም በመነሻ ጽሁፉ ላይ ቀርቧል።
መነሻ ፅሁፉንም ተከትሎ ከነዋሪዎቹ የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶች እየተነሱ ሲሆን፥ ነዋሪዎቹ በምንሰራበት ተቋማት እና በምንኖርበት ስፍራ ላይ ጥቃት ሲፈፀም ዝም ብለን ማየት የለብንም ብለዋል።
በከተማዋ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴአቸው ላይ ተፅእኖ ፈጥሮባቸው እንዳለፈም ነዋሪዎቹ አንስተዋል።
ነዋሪዎቹ በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን መስራት አለበት የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል።
የጥፋት ሀይሎቹም በህግ ተጠያቂ መደረግ አለባቸው የሚለውም ከተሳታፊዎቹ ተነስቷል።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፥ የከተማ አስተዳደሩ ውስጡን ምን ያክል እየፈተሸ ነው ወይ እና ሁከቱ በሚነሳበት ጊዜ መንግስት ለምን አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሁከቱን በቁጥጥር ስር አላዋለም የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ አራርሳ መርደሳ በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፥ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ውይይት የጥፋት ሀይሎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባና ህብረተሰቡን የማይወክሉ እንደሆኑ ከስምምነት መደረሱን አንስተዋል።
ሁከት ፈጣሪ ሀይሎችን ለምን ቶሎ መቆጣጣር አልተቻለም በሚል ለተነሳው ጥያቄም፥ ሁከት ፈጣሪዎቹ ድርጊቱን በተቀነባባረ መልኩ በአንድ ጊዜ ሲያካሂዱ ስለነበረ ቶሎ ለመቆጣጣር አስቸግሮ ነበር ብለዋል።
እንዲሁም ህብረተሰቡ በጊዜው የሁከት ሀይሎችን ለመከላከል ያሳየው ትብብር አነስተኛ ስለነበር ሁከት ፈጣሪዎቹ ከህብረተሰቡ ጋር በመመሳሳል ጥፋት መፈፀማቸውም አስቸጋሪ አድርጎታል ነው ያሉት።
በአሁኑ ጊዜ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ማጣራት እስካሁን 1 ሺህ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ያሉት ከንቲባው፥ በቀጣይም አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ለህግ እዲቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በከተማዋ በተከሰተ ሁከት ከፍተኛ 11 ፋብሪካዎች እና 62 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።
የተቃጠሉት ፋብሪካዎች ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩም ነበሩ።