Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በመቶዎች የሚቆጠሩ በሁከት የተሳተፉ ግለሰቦች በመመሪያው መሰረት እጃቸውን እየሰጡና የዘረፉትን የጦር መሳሪያ እያስረከቡ ነው- ኮማንድ ፖስቱ

surrender
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት በመላው አገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም የተደራጀው ኮማንድ ፖስት ከህዝቡ እያገኘ ባለው ድጋፍና ትብብር ተጨባጭ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን ገለፀ።

ኮማን ፖስቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በተለይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያ አንቀፅ መሰረት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፤ ጎንደር ከተማና አከባቢው ሸፍተው ጫካ የገቡና ከአሸባሪ ሀይሎች እናታጣቂዎች ጋር ሲገናኙ ከነበሩት ውስጥ በአከባቢው ህዝብ ድጋፍ እና ትብብር 93 ሰዎች በአከባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ሀይል እጃቸውን ሰጥተው መግባታቸውን እና ከእነዚህ ውስጥ 45 ከነሙሉ ትጥቃቸው እና 38 ደግሞ ያለ ትጥቅ የገቡ መሆናቸውን ነው ያመለከተው።

በኦሮሚያ ክልል ቄሌም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማና ሰዶ ወረዳ ዙሪያ ከተለያዩ ቦታዎች ተዘርፈው የተወሰዱ በቁጥር 70 የሚደርሱ የጦር መሳሪያዎች በራሳቸው በዘራፊዎቹ እና በህብረተሰቡ ጥቆማ ለፀጥታ ሀይሎች አስረክበዋል ብሏል መግለጫው።

በተመሳሳይ በቄሌም ወለጋ ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል በአከባቢው ህዝብ የማጋለጥና የመጠቆም ስራ እስካሁን 110 ሁከተኞች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እና ተደብቀው የቀሩትን ሁከተኞች ለመያዝ የክትትል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ምእራብ አርሲ ዞን በተፈጠረው ሁከትና በህዝብ ንብረትና የልማት ተቋማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ውድመት ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በህዝቡ ትብብርና ጥቆማ በሻሸመኔ ከተማ 450 እና በምእራብ አርሲ ወረዳዎች 670 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ተመልክቷል።

በተመሳሳይ በምእራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ከተዘረፈው 162 የጦር መሳሪያዎች ውስጥ በአገር ሽማግሌዎች ጥረት እና በራሳቸው ፈቃድ 88 ያህሉ ተመልሷል የሚለው ኮማንድ ፖስቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መግለጫ፥ የቀረውን የጦር መሳሪያ እና ከመንግስት፣ ከግልና ከልማት ተቋማት የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ ጥረቱ ቀጥሏል ብሏል።

በምእራብ ጉጂ ዞን ከተዘረፉት የጦር መሳሪያዎች እና ከህዝብ ተቋማት የተወሰዱ ቁሳቁሶች መካከል 32 ክላሺንኮቭ የተመለሰ ሲሆን፥ ቀሪዎቹን የማስመለስ ስራ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚሁ ዞን የተፈጠሩ ሁከቶችን በማስተባበር ግንባር ቀደም ከነበሩት መካከል በአከባቢው ህዝብ ጥቆማና የማጋለጥ ስራ 302 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ እና 20 የሚሆኑ ደግሞ በአዋጁ የአፈፃፀም መመሪያ የጊዜ ገደብ መሰረት በፈቃዳቸው እጃቸውን ለመስጠት ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉም ነው ያለው።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳማ፣ ቦራ፣ ሎሜ ሊበን ጭቋላ፣ አደአ፣ ቦሰትና አዳሚ ቱሉ በተባሉ ወረዳዎች በተፈጠረው ሁከት ከተዘረፉ 92 ዘመናዊ እና ኋላቀር የጦር መሳሪያዎች እና ስምንት ሽጉጦች ተሰብስቧል።

በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካላት ከተዘረፈው 513 የተለያየ ዓይነት የጦር መሳሪያ ውስጥ እስካሁን ድረስ በተደረገ እንቅስቃሴ 384 ያህሉ ተመልሷል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፈፃፀም መመሪያ አንቀፅ 4 ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍም በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ 13 የሚሆኑ ነጋዴዎች፣ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ውስጥ ውስጡን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሌሎች 13 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከትምህርት ገበታ ሆነ ብለው በመቅረት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሞከሩ ሶስት አስተማሪዎች ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመልክቷል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ እና ህዝቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 35 ነጋዴዎች መካከል ስድስቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ ሲለቀቁ የቀሩት 29 የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ብሏል።

ኮማንድ ፖስቱ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረ ሁከት በቡድን ወይም በግል የተሳተፈ፣ የጦር መሳሪያ ወይም ማንኛውንም የግልም ሆነ የመንግስት ንብረት የዘረፈ፣ ለህገወጥ ተግባራት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ፣ ወረቀት በመበተን አድማ በማድረግ የተሳተፈና ያነሳሳ እንዲሁም ሰው የገደለ፣ ማንኛውንም ንብረት ያቃጠለና ወንጀል የፈፀመ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የእርምጃ አፈፃፀም መመሪያ አንቀፅ 31 መሰረት የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ከማለቁ በፊት በቀሩት አምስት ቀናት ውስጥ በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እጁን እንዲሰጥና የዘረፈውን ንብረት እንዲያስረክብ አሳስቧል።