አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 20 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁከት እና ነውጥ ድርጊቶች ተሳታፊነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች የሚገኙባቸው ማዕከላት ይፋ ሆኑ።
በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት እና ነውጥ በመደበኛ የሰላም እና ህግ ማስከበር አካሄድ ለመመከት ባለመቻሉ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሀገሪቱን ህዝቦች የሰላም እና ደህንነት ስጋት መቅረፍ መቻሉን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ተናግረዋል።
አቶ ሲራጅ ለአዋጁ ውጤታማነትና ሁከት እና ነውጦችን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም፥ የሀገሪቱ ህዝቦች ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ያደረጉት ትብብር ዋና ምክንያት መሆኑንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ፥ ከ400 በላይ ተጠርጣሪዎች በሁከት እና ነውጥ መሳተፋቸውን አምነው እጃቸውን መስጠታቸውንም ነው ያነሱት።
ከዚህ ባለፈም ከ1 ሺህ 500 በላይ የጦር መሳሪያዎች ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ባደረገው ትብብር ተመልሰዋልም ብለዋል።
የመከላከከያ ሚኒስትሩ፥ በኦሮሚያ ክልል ሁከት እና ነውጥ በተከሰተባቸው ቀናት የተዘረፉ የግለሰቦች እና የመንግስት ንብረት የሆኑ በርካታ ቁሳቁሶች በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በሁከቱ ተሳታፊ በነበሩ ግለሰቦች ፈቃደኝነት ለባለቤቶቹ ተመልሰዋል ነው ያሉት፤ ይህም የመመሪያው ድንጋጌ አንድ ውጤት መሆኑን በመጥቀስ።
በራሳቸው ፈቃድ በሁከት ድርጊቶች መሳተፋቸውን አምነው እጃቸውን ከሰጡ ግለሰቦች ባሻገር፥ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በመያዝ በኩል የተወሰደው እርምጃ በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ እንጂ ጅምላ አፈሳ አለመፈጸሙንም ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደት በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ማንነት እና የሚገኙበት የማረሚያ ስፍራም፥ ባለፈው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
የሀገሪቱ ህገ መንግስትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ መሆን እንዳለበት ያስገድዳል።
አቶ ሲራጅ በመግለጫቸው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎች እና በአዲስ አበባ በቁጥጥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ትምህርት እና እርምት እያገኙባቸው ያሉ ማዕከላትንም ይፋ አድርገዋል።
በዚህ መሰረት ኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ፣ ሰሜን ሸዋ እና ምስራቅ ሸዋ ዞን አካባቢ የተያዙ ተጠርጣሪዎች በአዋሽ ማዕከል፥ እንዲሁም በጉጂ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ሃረርጌ ዞኖች እና በባሌ ዞን አካባቢ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ዝዋይ አላጌ ማዕከል እንደሚገኙ ተገልጿል።
በተጨማሪም በቄለም ወለጋ፣ ምእራብ እና ምስራቅ አርሲ ዞኖች እንዲሁም በምእራብ ሸዋ እና ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን የተያዙ ተጠርጣሪዎች ጦላይ በሚገኝ ማዕከል ይገኛሉ።
በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን የተያዙት በዲላ ከተማ፣ በአዲስ አበባ የተያዙ እዛው አዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ በምእራብ ጎጃም እና አዊ ዞን የተያዙ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በባህርዳር ከተማ በሚገኙ ዞኖች የተሃድሶ ትምህርት እያገኙ መሆኑ ተነግሯል።
በማቆያ እና የእርማት ማእከላት የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ በአግባቡ መያዛቸውን ያነሱት አቶ ሲራጅ፥ በቀጣይ በምን መልኩ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት እንዳለባቸው ይፋ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ብዛት በመርማሪ ቦርዱ ይፋ እንደሚሆን የገለፁት አቶ ሲራጅ፥ በተጠርጣሪነት ተይዘው ከነበሩ ግለሰቦች መካካል 2 ሺህ ያህል ተጠርጣሪዎች ትምህርት እና ምክር አግኝተው መለቀቃቸውን ጠቁመዋል።
በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብርበራን ተገን በማድረግ ዝርፊያ እየተፈፀመ ነው በሚል ለተነሳው ጥያቄ፥ በጣም ጥቂት በሚባሉ የፖሊስ አባላት እና የፀጥታ ሃይሉን የደንብ ልብስ በለበሱ ግለሰቦች በተለያዩ አካባቢዎች ዝርፊያ መፈፀሙን ጥቆማ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ እስከ አራት የሚደርሱ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው የተናገሩት።
ህብረተሰቡ እንዲህ ያለ ጉዳይ ሲገጥመው፥ በ816 እና 987 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማዎችን ማድረስ ይችላልም ብለዋል።
አቶ ሲራጅ በመግለጫቸው ማጠናቀቂያ፥ ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ሆኖ በሰራው ስራ ሀገሪቱ የልማት እድገቷን ሊያስቀጥል ወደ ሚያስችል የቀደመ ሰላም እና መረጋጋት እየተመለሰች ነው የሚል ማረጋጫን ሰጥተዋል።