አዲስ አበባ ፣ መስከረም 8 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ባለፈው ሀሙስ ምሽት በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረታቸው የወደመባቸውን ነዋሪዎች መልሶ ስራ ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ አቶ ሲሳይ አዳነ እንዳሉት፥ ሱቆቻቸውና ንብረታቸው ከወደመባቸው ነጋዴዎች ጋር ውይይት ተደርጎ ስራ ለመጀመር የሚያስችሉ በእሳት የወደመውን የገበያ ቦታ የማፅዳትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
በዚህም ጊዜያዊ ሼድ በመገንባት ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል አቶ ሲሳይ፡፡
ከሚገነባው ጊዜያዊ ሼድ ጎን ለጎን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
እንደ ምክትል ሃላፊው ከነጋዴዎቹ ጋር በተደረገ ውይይት በእሳት የወደመውን ንብረት መጠን የማጣራት ስራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ባለፈው ሀሙስ ምሽት በተለምዶ ቅዳሜ ገበያ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ቦታ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ400 በላይ የአልባሳት፣ የብረታ ብረትና ቅመማ ቅመም ሱቆች መውደማቸው ይታወሳል፡፡
የአደጋው መንስኤ በመጣራት ሂደት ላይ መሆኑን የጎንደር ፋና ኤፍ ኤም ባልደረባችን ነብዩ ዮሐንስ ዘገባ ያመለክታል።