አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአምስት ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በተያዘው አመት መጨረሻ ይጠናቀቃል አለ የትምህርት ሚኒስቴር።
በሚኒስቴሩ የአስራ አንዱ ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ክፍሌ፥ የሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በተያዘው አመት መጋቢትና ሚያዝያ ወር ድርስ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል።
ግንባታዎቹ ዘገዩ ከተባለ ግን ሁሉንም እስከ ሰኔ ወር ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ሳሙኤል የጠቆሙት።
ስራ አስኪያጁ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በ2010 አመተ ምህረት ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ይጀምራሉ ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በተሟላ ሁኔታ የመማር ማስተማሩን ሂደት እንዲያካሂዱም አስፈላጊ የተባሉ የላብራቶሪ፣ የመመገቢያ እና ሌሎች ለመማር ማስተማሩ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ጊዜያት በተለይም በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚታየውን የኢንተርኔት፣ የመብራት፣ የውሃ እና የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት እጥረቶች በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችም ላይ እንዳይከሰቱ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው አቶ ሳሙኤል ያነሱት።
በ2010 አመተ ምህረት ማስፋፍያ ከሚሰራላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውጪ ያሉ ዘጠኙ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያ ዙር ቅበላቸው 1 ሺህ ተማሪዎችን ተቀበለው ያስተናግዳሉ ነው ያሉት።
በአጠቃለይ በቀጣዩ አመት ዘጠኙም ዩኒቨርስቲዎች በመጀመርያው ዙር ብቻ 16 ሺህ 50 መቶ ተማሪዎችን ይቀበላሉ።
ይህም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ላይ በአንድ ጊዜ እስከ 7 ሺህ ተማሪዎችን የሚይዙ ዩኒቨርሲቲዎችን የመገንባት እቅድ የሚያሳካ ነው ብለዋል።