አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 2008 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ሁነቶችን አስተናግዷል።
አመቱ እንደ ሀገር ስኬት የተመዘገበበት ፈተና ያጋጠመበትም ነበር።
ድርቅ
የብሪታንያው ጋዜጣ ዘጋርዲያን በብሪታንያው ቢቢሲ ላይ ተሳለቀ፤ ኢትዮጵያ ከሰባ ሰባቱ በባሰ ድርቅ ብትመታም ቢቢሲ እንደ 77ቱ ያለ ሞትን አጣ ሲል ፃፈበት።
ይህ ከ2008 ክዋኔዎች ሁሉ ጎልቶ የሚነሳ ሁነት ነው።
በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ስዩም መስፍንም አምና ሊባል ሁለት ቀናት የቀሩትን አመት ኢትዮጵያ ተፈትና ያለፈችበት ይሉታል።
መንግስት እና ህዝብ የገነቡት አቅም በተምሳሌትነት እንድትወደስ አድርጓታል ያሉት አምባሳደር ስዩም፥ በድርቁ የሀገሪቱ ዜጎች እንዳይሞቱ እና ከቀያቸው እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ የተሰራው ስራም ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።
10 ነጥብ 4 ሚሊየን ህዝብ ለድርቅ ተጋልጦ አንድም ሰው ለሞት አለመዳረጉን ያዩ ሀገራት የሀገሪቱን ጥንካሬና ኢትዮጵያ ለተፈጥሮ አደጋ የማትንበረከክ ስለመሆኗ ለመናገር ደፈሩ ይላሉ አቶ ስዩም።
ጎርፍ
በፀሃይ ደርቃ የነበረች መሬት የማትሸከመው የዝናብ ዶፍ ወረደባት፤ ውሃ አጥተው የነበሩ ወንዞችም በውሃ ሙላት መገንፈል ጀመሩ።
በድርቅ ስትታመስ የነበረችው ሀገርም ጥቂት ስፍራዎቿ በጎርፍ ተመቱ።
ለረሃብ እጅ ያልሰጡ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ተነጠቁ።
ሁከት
ህዝብ በመንግስት ላይ ተቃውሞውን አሰማ።
ተቃውሞቹም ወደ ሁከት ተለውጠው ለሰው ህይወት መጥፋት ለንብረት መውደምም መንስኤ ሆኑ።
አሮጌ ሊባል 48 ስአታት የቀረው 2008 በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሁከቶች ተስተናገዱበት።
አመቱ ሊጠናቀቅ ወራት ሲቀረው ሀገሪቱን የሚመራው ድርጅት በውስጤ ብልሽት አለ ብሎ አወጀ።
የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ከበደ ጫኔ እንደሚሉት፥ 2008 ከድርጅቱ አንደበት ውስጤ ይፅዳ የሚል ድምፅ ተሰምቶበታል።
ቤቴን አፀዳለሁ ያለው ድርጅት እና መንግስት ለውሳኔው የራሱ ግምገማም ነበረው።
ዘመን በጊዜ እንደሚታደስ አዲስም አመት አዲስ ተስፋን ይዞ እንደሚመጣ 2008 የመታደስ ጅማሮ አደረኩ ለሚለው ድርጅት 2009 መታደስ እስከምን ድረስ የሚል ጥያቄ አለው።
የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በ2009 የሚተገበረው መታደስ አላስፈላጊ አካልን በጥሶ እስከ መጣል የሚል ምላሽ አላቸው።
ኢህአዴግ በራሱ ላይ የተለጠፉ ጠባብነት፣ ትምክህት እና ኪራይ ሰብሳቢነትን በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማስወገድ ከቻለ ኢህአዴግ መታደስ ይችላል፤ ለዚህም ድርጅቱ ቁርጠኛ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
የ2009 የትኩረት አቅጣጫዎች
አምባሳደር ስዩም መስፍን “ከእንግዲህ ከህዝቡ ጋር ግልፅ፣ ጠንካራ እና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ይኖረናል፤ ህዝባችንን አናዳምጥም ካልን የሚሸከመን ህዝብ አይኖርም፤ የመንግስትን ስልጣን ህዝቡን ለማገልገል ካልተጠቀምንበት አወዳደቃችን አያምርም” ብለዋል።
አዲስ አመት ምድርን አደይ አበባ አልብሶ እንደሚያድሳት ሁሉ፤ ስራ ፈተው አመታት የተቀመጡ እጆች በአዲስ አመት ስራን ይጠይቃሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ አባይ ፅሃዬ፥ አዲሱ አመት የወጣቱ የተስፋ አመት ይሆናል፤ ወጣቶች ራሳቸው ከሚፈጥሩት ስራ ባሻገር በመንግስት እና በባለሃብቶች ሰፊ የስራ እድሎችም ይፈጠራሉ ብለዋል።
ወጣቶች ተደራጅተው ስራ እንዲፈጥሩም መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቧል ነው ያሉት።
ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ከተወጣ ሀገሪቱ ሰላሟ ብቻ ሳይሆን ተስፋ የፈነጠቀው ልማት፣ እድገት እና ዴሞክራሲ ይጎለብታል፤ ኢትዮጵያ አሁንም ተረጋግታ ትቀጥላለች ብለዋል አቶ አባይ።