Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

አዲሱ ዓመት ካጋጠሙ ችግሮች ወጥተን ልማታችንን በስፋት የምናፋጥንበት ሊሆን ይገባል- አቶ ገዱ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲሱ ዓመት ባለፉት ቀናት ካጋጠሙ ችግሮች ወጥተን ልማታችንን በስፋት የምናፋጥንበት ሊሆን ይገባል አሉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው።

ርዕሰ መስተዳደሩ የ2009 አዲስ ዓመትን በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ለክልሉ ህዝብ እና ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል።

አሮጌው ዓመት በርካታ የልማት እና የመልካም አስተዳዳር ስራዎች የተሰሩበት ቢሆንም፤ ህዝቡ በሚፈልገው ያክል እንዳልሆነ የክልሉ መንግስት ያምናል ሲሉም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

አዲሱ ዓመት የህዝብ ጥያቄ በስፋት የሚመለስበት እና የተሻለ እርካታ በሚፈጠርበት ደረጃ የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ይሰራል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም ባለፉት ቀናት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከት በጠፋው የሰው ሀይወት እና በደረሰው የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት መውደም የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል።

ችግሩ ከዚህ እንዳይባባስ የመከላከል ስራውን የሰራው የክልሉ ህዝብ እና የፀጥታ ሀይል ምስጋና ይገባዋል ሲሉም አቶ ገዱ በመግለጫቸው አያይዘው ተናግረዋል።

“በአዲሱ ዓመትም ይህን የተጠናከረ ተግባር ይዘን፤ በተባበረ ክንዳችን የተሻሉ ለውጦችን የምናይበት እንዲሆን መልካም ምኞቴ ነው” ብለዋል።

በሀይለኢየሱስ ስዩም
gedu-9816