መስከረም 2009 ዓ.ም
ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር
ጉዳዩ: ተጠያቂነት ስለመኖር
በቅርቡ የተሳሳተ ካርታ እና ያልሆነ መረጃ ያካተቱ የመማሪያ መጽሕፍቶች ታትመው ለጥቅም እንደዋሉ በማመን ለተፈጠረው ስህተት የትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ መጠየቁ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመልክተናል። እንደ ተቋም ለተፈጠረው ግድፈት ሃላፊነት ወስዶ በኣደባባይ ይቅርታ መጠየቁ እናደንቃለን። ያም ሆኖ ግን ልዩ ሙያዊ ሃላፊነት የሚወስዱ ባለ ሙያዎች እና የስራ ሃላፊዎች ሊኖሩ ይገባል እንላለን። ለመሆኑ እንዴት ይሄን የሚያክሉ ግዙፍ እና ግልጽ የሆኑ ግድፈቶች ሊፈጸም ቻሉ? በኛ እምነት ይህ ተራ ስህተት ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ኣውሎ ችግር ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ኣደገኛ ሴራ ነው። ስለሆነም ለሌሎችም ኣስተማሪ ይሆን ዘንድ በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ በለሙያዎች እንደየ ሃላፊነታቸው በህግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል እንላለን።
ይህ ብዙ ደም የማፋሰስ ኣደጋ ሊያስከትል የሚችል የነበረ ከባድ ወንጀል እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ጃፓን እና ቻይና፣ ፊሊፒን እና ቻይና፣ ቬትናም እና ቻይና፣ እስራኤል እና ፍልስጥኤም በተለያየ ጊዜ ባሳተሙዋቸው የትምህርት መማሪያ መጽሃፍቶች ላይ የሰፈሩት የካርታ እና የመረጃ ይዘት ምክንያት በተደጋጋሚ ለግጭት መዳረጋቸውን ይታወሳል። በእኛ ኣገርም ምንም እንኳ በክልሎች መካከል ያለ ጉዳይ ቢሆንም በኣገራችን ያለውን የስርኣት ድክመት እና የፖለቲካ ጽንፈኝነት ከግምት በማስገባት ቀላል የማይባል ኣደጋ ሊያደርስ የሚችልበት እድል እንዳለ ብዙ ማስያዎች ኣሉ።
ለምሳሌ ይህ የተሳሳተ ካርታ ባልታወቀበት ሁኔታ እንኳን ኣገሪቱ በሁሉም ኣካባቢዎች የኣዋሳኝ ቦታዎች ግጭት ኣስተናግዳለች። በኣፋር እና በኣማራ፣ በኣማራ እና በኦሮሚያ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ህዝቦች ክልል፣ በትግራይ እና በኣማራ፣ በእሮሚያ እና በሶማሊ ክልሎች ኣዋሳኝ ቦታዎች ላይ ሞቅ በረድ የሚሉ የቆዩ የወሰን ግጭቶች እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚህ ኣንዳንዶቹ በውስጥና በውጭ ያሉ የጽንፈኛውን የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ እና ማወናበድ ታክሎባቸው ደም ያፋሰሱ ግጭቶች ሲሆኑ ኣንዳንዶቹ ግን በኣካባቢ ሽማግሌዎች እና የመንግስት ጣልቃ ገብነት ብዙም ችግር ሳያደርሱ ለመፍታት የተቻለበት ሁኔታ እናያለን። በተመሳሳይ ለብዙ ዜጎች ሂወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን የኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን ያየን እንደሆነም በኣንድ በኩል የመንግስት ግልጽነት መጓደል የፈጠረው በሌላ በኩል ደግሞ ኣካባቢውን የሚያስተዳድሩ ብልሹ የመንግስት ባለስልጣናት እና ሰላም የማይፈልጉ የጥፋት ሃይሎች ባደርጉት የማወናበድ እንቅስቃሴ ብዙ ጥፋት ኣድርሶ ወደ ሌላ ኣድማና ቀውስ የተሸጋገረበት ሁኔታ እናያለን።
በዚህ ካርታ እንደሚታየውም ስህተቱ በኣንድ ክልል የተወሰነ ሳይሆነ ሁሉንም ክልሎች የነካ በመሆኑ ግጭት ቢነሳ ሁሉም ክልሎች የሚያዳርስ ይሆናል። ኣላማውም የውዝግብ ፖለቲካ ፈጥሮ የሚጠሉትን መንግስት ላይ ተጨማሪ ፈተና ለመጫን የተቀነባበረ ሴራ ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም የኣገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግስት ኣካላት የጉዳዩን ኣሳሳቢነት እና የሚያስከትለውን መዘዝ ከግምት በማስገባት ሚኒስትሪው ከሰጠው ማብራሪያ እና ይቅርታ ባሻገር ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን በመለየት በህግ ሊያስጠይቃቸው ይገባል እንላለን።