Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የብሄር ብሄረሰቦች እና የቱሪስቶች ማዕከል በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ ሊገነባ ነው

nation-and-nationalities
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ የብሄር ብሄረሰቦች እና የቱሪስቶች ማዕከል በአዲስ አበባ እንጦጦ ተራራ ላይ ሊገነባ ነው።
በ1 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችን ለጎብኝዎች ለማስተዋወቅ፥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይገልጻል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ገብረጻድቅ ሀጎስ ማዕከሉ በከተማዋ የሚመጡ ጎብኝዎች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ያደርጋል ይላሉ።
በ114 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል መሉ ወጪው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሸፈን ሲሆን፥ የግንባታ እና ዲዛይን ጥናቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከ 2 ዓመት በፊት ተጠናቋል።
ባህል ማዕከሉ የብሄር ብሄረሰቦችን አለባበስና የአለባበስ ስርዓት፣ ውዝዋዜና የተለያዩ ባህላዊ የጋብቻ ስነ ስርዓቶችን ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ለጎብኝዎች የሚቀርቡባቸው ህንፃዎችንም ያካተተ ነው።
ማዕከሉ የተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ከእንጨት የተሰሩ የኢትዮጵያውያንን ባህል የሚያንፀባርቁ ቁሳቁስ እና ጌጣጌጦች፥ ለሽያጭ እና ለእይታ የሚቀርቡባቸው ህንጻዎችንም ያካትታል ተብሏል።
በተጨማሪም ጉብኝዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱባቸው የባህል እና ዘመናዊ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም በማዕከሉ ተካተዋል።
ይህ መሆኑም የሀገሪቱን ገጽታ በተሻለ መንገድ ለማስተዋወቅ ይረዳል ነው ያሉት የቢሮ ሀላፊው አቶ ገብረጻድቅ።
መዳረሻ ማዕከሉን በልዩ ትኩረት ለመምራትና ለመገንባት እንዲያስችልም ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ሀላፊ ዶክተር ሂያብ ገብረፃድቅ እንዳሉት፥ እንጦጦ በተፈጥሮ ሀብቶች የተከበበ ስፍራ እንደመሆኑ መጠን ማዕከሉ ሲገነባ ሀገር በቀል ዛፎችን እና እጽዋትን በመትከል ተፈጥሯዊ ውበትን የተላበሰ እንዲሆን ይደረጋል።
በያዝነው አመት የሚጀመረው የማዕከሉ ግንባታ ከአምስት አመታት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።