Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ ጥናት ከሚያካሂዱት ኩባንያዎች ጋር ሊፈራረሙ ነው

image
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 26፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ቴክኒካዊ ጥናት ከሚያካሂዱት ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር በቅርቡ ስምምነት እንደሚያደርጉ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ስምምነቱ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሚካሄደው የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እንደሚከናወንም ይጠበቃል።

ሦስቱ አገራት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ ሊኖረው የሚችል አሉታዊ ተጽፅኖ ካለ ጥናት ከሚያካሂዱ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ያደርጋሉ።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2013 የተቋቋመው የሦስትዮሽ ቴክኒክ ኮሚቴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖ የሚያጠኑ ኩባንያዎችን መምረጣቸው ይታወሳል።

ግብጽ “ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የውሃ ድርሻ መጠን ይቀንስብኛል” በሚል ስጋቷን ስትገልጽ የቆየች ቢሆንም ኢትዮጵያ ግድቡ የግብጽንና የሱዳን የውሃ ድርሻ ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንደሌለው በተደጋጋሚ ስታስረዳ ቆይታለች።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት፥ ቀደም ሲል ከግብፅ በኩል የሚነሳውን ስጋት ለመቀነስና የበለጠ መተማመን እንዲፈጠር ከሦስቱም አገሮች ስድስት ባለሙያዎችና አራት ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ከግድቡ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድኑም የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የግንባታውን አጠቃላይ ሁኔታና የደረሱበትን ጥናት ለአገራቱ አሳውቀዋል።

ባለሙያዎቹ ግድቡ ውሃ ሲይዝና ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በታችኞቹ የአባይ የተፋሰስ አገራት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አከባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖም እንዲጠና ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል።

ሦስቱም አገሮች የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረው ጥናቱ እንዲከናወን ሁኔታዎች ሲያመቻቹ እንደቆዩም ነው አቶ ብዙነህ የተናገሩት።

ከሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች መካከል ቢአርኤል በዋና አጥኚነት (70 ከመቶ) ፥አርቴሊያ ደግሞ ንዑስ ኮንትራት ከቢአርኤል በመውሰድ (30 በመቶ) ጥናቱን የሚያካሂዱ ይሆናል።

አቶ ብዙነህ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ሶስቱ አገሮች ለመጠናቀቅ እየተቃረበ ባለው ሰነድ ላይ በተለያዩ ጊዜያት እየተወያዩ ጥናት ለማስጀመርያና የመጨረሻ ፊርማቸውን ለማኖር ተቃርበዋል።

ኩባያንዎቹ ጥናቱን ለማካሄድ ዝግጅት የጨረሱ መሆኑ በቅርቡ ከአገራቱ ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ ይገባሉም ነው ያሉት።

ከ15 ቀን እስከ 1 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ኮንትራት ዶክመንቱ ተፈርሞ ኩባንያዎቹ ወደ ጥናት እንደሚገቡና በ11 ወር ጊዜ ውስጥ ጥናታቸውን አጠናቀው ለሶስቱም አገሮች ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን የግድቡ የውሃ አያያዝና አለቃቀቅ፣ ኃይድሮሎጂካል ሲሚዩሌሽን ሞዴልና ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ሊያመጣ የሚችለው ተጽእኖ ካለ እንዲጠና ከዓመት በፊት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ሁለቱ ኩባንያዎች ጥናቶቹን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ በ70/30 ክፍፍል የሚያከናውኑ ሲሆን ወጪው በሶስቱ አገሮች እኩል መዋጮ እንደሚሸፈን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።