አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ጠጥቶ ማሽከርከርን ለመቆጣጣር በትንፋሽ መመርመሪያ መሳሪያ የታገዘ የትራፊክ ቁጥጥር የሙከራ ስራ ማከናወኑን የመዲናዋ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ ብሉምበርግ ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ከተባለ ተቋም ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሰለሞን ኪዳነ፥ ጠጥተው የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት መሣሪያ በተግባር ላይ ለማዋል ሙከራ ተደርጓል ብለዋል።
ሙከራው በእንግሊዝ ኤምባሲ፣ በዑራኤል እና በካዛንቺስ አካባቢዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወኑንም አስራ አስኪያጁ ስታውቀዋል።
የትንፋሽ መቆጣጠሪያ መሣሪያው ኅብረተሰቡ በመወያያ መድረኮች፣ በመገናኛ ብዙኃንና በቢልቦርድ ግንዛቤውን በመስጠት ከ4 ሳምንታት በኋላ ሥራ ላይ እንደሚውል ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
ጽህፈት ቤቱ መሣሪያውን ወደ ሥራ ከማስገባት በተጓዳኝም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ጋር በመቀናጀት ለባለድርሻ አካላትና ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ለዚህም 20 አሽከርካሪው የወሰደውን የአልኮል መጠን የሚያመለክቱና 45 አሽከርካሪው አልኮል መውሰድ አለመውሰዱን የሚያረጋግጡ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ50 በላይ ባለሙያዎች በዘርፉ ስልጠና መስወዳቸውን ስራ እስኪያጁ አብራርተዋል።
መሳሪያው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ የተገኙ አሽከርካሪዎች ባሉበት ቁልፍ አስረከበው እንደሚሄዱና ተሽከርካሪው በሌላ አካል እንደሚነሳም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
ከአቅም በላይ አልኮል ተጠቅመው ሲያሽከረክሩ የሚገኙ አሽከርካሪዎች በሕግ ይጠየቃሉም ብለዋል።