Alpha Negari Contributor Tekle Abadi (Mekele ,Tigray 22/9/2016). ለስድስት ቀናት (ከዕለት 05 – 11/01/09 ዓ/ም እሁድ ዕለት ሳይጨምር) ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ‘የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ እና አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ መፍጠር’ ላይ ነበር፡፡ ስልጠናው በዶ/ር ክንደያ፣ ዶ/ር አዲሰአለም እና አቶ ንጉሰ ነበር የተሰጠው፡፡ ስልጠናው ጠዋት ጠዋት በአሰልጣኞች ማብራርያ እና ከሳአት ደግሞ በየኮሌጁ ጥያቄ እና አስተያየት በመስጠት ነበር የተከናወነው፡፡
ዶ/ር አዲሰአለም ‘የ20 ዓመት የስኬት ምንጭ’ እና ‘አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ በመፍጠር’ ላይ በሁለት ቀናት ቆይታቸው ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የ20 ዓመት የስኬት ምንጭ ብለው ከጠቀስዋቸው ክንውኖች አንዱ እንዲህ ይላል፡-
ዓለም ዓቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማት ይሁን ሃያላኑን መንግስስታት ምክረሐሳብ ሳንቀበል ለተጨባጩ የሃገራችን ችግር መፍትሔ ማምጣት የሚችል በዚህም ህዝባችን ከድህነት የሚያላቅቅልን ርእዮት በቂ ሳይንሳዊ ትንተና በማድረግ ከሌሎች ልማታዊ መንግስታት ተመኩሮ በመማር ከልምዳችን ችግራችን በማረም ያሳካነው ውጤት ነው፡፡
ዶ/ር አዲሰአለም በሰጡት ማብራርያ መሰረት በማድረግ ከተጠየቁ ጥያቄዎች የሚከተሉትን ይገኙባችዋል፡-
1. አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ ለመፍጠር መንግስት ምን እየተሰራ ነው? ለምሳሌ በትግራይ ክልል ምን የታሰበ ነገር አለ?
2. አንድ ክልል የሌላ ክልል ሸክም አድርገው ለሚያስቡ ሰዎች እንደ መልስ ሊያገለግል የሚችል ስተራተጂ ነድፈን መስራት የለብንም ወይ? ለምሳሌ የትግራይ ክልል የማይኒነግ የልህቀት ማእከል ማድረግ ኦሮምያ ደግሞ የእርሻ እና የእርሻ ውጤት ማእከል በማድረግ፡፡
3. በትግራይ ክልል ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብት የለም፣ የክልሉ መንግስትም ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ አያበረታታም፣ ለምን እንዲህ ይሆናል? ለምሳሌ የወረዳ መሆን እንፈልጋለን ጥያቄ ህዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ እንዳይጠይቅ ተከልክለዋል፡፡
4. የትግራይ ክልል የዩኒቨርስቲ ተማሬዎች ወደ አማራ ክልል የዩኒቨርስቲዎች ሄደን አንማርም እያሉ ነው፡፡ የሁን እንጂ ይህ ተግባር አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ የመፍጠር ስትራተጅያችን ስለ ሚቃረንና የነበረውን ነባራዊ ሃገራዊ ስብጥር ስለ ማይገልጥ ሄደው እንዲማሩ እናረጋለን እያላችሁ ነው፡፡ ይህንን ስታደርጉ የተማሬዎች ድህንነት ለመጠበቅ ምን ምን ስራዎች እየሰራችሁ ነው?
5. የድሮው ኢህአዴግ አለ ወይ? ብአዴን የሚባለው ፓርቲ እንደ የኢህአዴግ አካል ሁኖ በእውነት ፋንክሽን እየሰጠ ነው ወይ?
6. የትግራይ ህዝብ እስከ መቼ ነው እየተበደለ፣ እየተባረረ፣ እየተገደለ፣ ንብረቱ እየተዘረፈ የሚኖረው? ለመሆኑ ይህንን ጥያቄ ተጠይቆ ያውቃልን?
ዶ/ር አዲሰአለም ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ አልሰጡባቸውም፡፡ በተለይም በሁለተኛው ቀን (06/01/09) አንድ ተሳታፊ ዶ/ር አዲሰአለም እያቀረቡ ሳለ እድል ሳየሰጣቸው በድንገት ከመቀመጫቸው በመነሳት ‘እናንተ ሁሌም የማዳመጥ ችግር አለባችሁ: ሁሌም መድረኩን ብቻችሁ ነው ምትቆጣጠሩት፣ ለ25 ዓመት ሙሉ ስናዳምጣችሁ ቆይተናል፣ የዩኒቨርስቲው ማህበርሰብ እነዲሳተፍ አታደርጉም፣ ለምንድ ነው እንዲህ የሚሆነው? ብሎ ዘለፋ በማዝነብ የስበሰባው መንፈስ በመረብሽ አቅራቢውም ያልጠበቁት ስለሆነ ነው መሰለኝ ፍራስተሬት ያደረጉ ይመስል ሲከተሉት የነበረው ሰፋ ያለ ማብራርያ የመስጠት ዘዴ በመተው ሰፊ የዘት ያለው ሃሳብ አጠር አድርገው ስያቀርቡት ተስተውለዋል፡፡ በመሆኑም ተሳታፊው ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ተገቢውን ክብር አልሰጡንም፣ የሰዓታት ማብራርያ የሚያስፈልገው ዶክዩመንት በ30 ደቂቃ ጨርሰዉታል የሚሉ ቅሬታዎች አስከትለዋል፡፡
ከሰጥዋቸው ማብራርያዎች ለመጥቀስ ግን ዶ/ር አዲሰአለም እንዲህ ብለዋል፡፡ አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ ለመፍጠር መንግስት ብዙ ስራዎች እየሰራ ነው፡፡ በየአከባቢው ያለ ማህበረሰብ የፈጣን ልማታችን ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ በትግራይ ክልልም ብዙ የልማት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ለምሳሌ በሑመራና በራያ አከባቢዎች የመካናይዝድ አግሪካልቸር ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በመቐለ አከባቢ ደግሞ የኢንዳስትርያል ዞኖች እየተስፋፉ ነው፡፡ ባለ ሃብቱም እያሳተፍነው ንው፡፡ ለምሳሌ
በመቐለ አከባቢ ለእንዳስትርያል ዞኖች የሼዲንግ ሰርቪስ የሚያቀርቡ ባለ ሃብቶች ፈቃድ ተሰጥዋቸው ስራ ጀምረዋል፡፡
አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ መገንባት የሚቻለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግላዊ እና ከባብያዊ ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ ለሃገራዊ ሰላም፤ እድገት እና ድህንነት ቅድምያ በመስጠት የፌድራል ስርዓቱን ለመናድ ሚንቀሳቀሱ ሃይሎች መንገዳችው ትክክል እንዳልሆነ በማመን እና በማሳመን ተግባር ላይ የሚተጋ ኢትዮጵያዊ መፍጠር ሲቻል ነው (የግሌ አስተያየት)፡፡ ዶ/ር ክንደያ የመቐለ ዩኒቨርስቲ ዓመታዊ የስራ ክንውን እና ቀታይ የስራ አቅጣጫዎች ከማቅረብ እና በዙርያው ላይ የተነሱ ጠያቄዎች እጅግ ማራኪ እና ብስለት በተሞላው መንገድ ካቀረቡ ብኋላ ማለትም ሃሳባቸው ስያጠቃልሉ እንዳሉት ፤ በቅርብ ጊዜ ያየናቸው እንደ የራስዳሽን እና አከባቢው እንዲሁም የበንሻንጉል ክልል ወደ ትግራይ ማለትም የህዳሴ ግድብ ወደ ትግራይ ማስገባት ዕቅድ እነዳለ የሚያሳይ ካርታ በመስራት እና ሌሎች ከእውነት የራቁ የስማ በለው መደናገርያ ክስተቶች ዋናው ዓላማቸው የፌድራል ስርዓቱ መናድ ነው፡፡ ይህ ተግባር አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ የመፍጠር ራእያችን ትልቁ ማነቆ ስለሆነ በአፋጣኝ ስር ነቀል ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡
አቶ ንጉሰ በ09/01/09 እና በ10/01/09 በትምህርት ልማት ሰራዊት ላይ ነበር ስልጠና እና ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት፡- ‘የሰራዊት ግንባታ ሥራና የትምህርት ጥራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን’፡፡ በመግብያቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡- ‘በየትኛው መስክ በየትኛውም ተቋም የሰራዊቱ ሚና ተቋማት ለተደራጁለት ዓላማና ተልዕኮ ማሳኪያ መጠቀም ይችሉ ዘንድ ሰራዊቱን ዋና የስበት ማዕከል እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ሠራዊቱ ከዚህ የተለየ ዓላማና ተልዕኮ ሊኖረውም ሊሰጠውም አይችልም፡፡’
አቶ ንጉሰ በሰጡት ማብራርያ መሰረት በማድረግ ከተጠየቁ ጥያቄዎች የሚከተሉትን ይገኙባችዋል፡-
1. አርሚ አልያም ሰራዊት የሚል ስም ወደ ዩኒቨርስቲ አምጥቶ መጠቀም ተገቢ ነውን? ለመሆኑ የልማት ሰራዊት አስፈላጊ ነው? ሌላ አማራጭ መጠቀም አንችልም ወይ?
2. የልማት ሰራዊት ግንባታ ስናካሂድ ለምን በአንድ ት/ት ክፍል ብቻ ይሆናል? ለምን በት/ት ክፍሎች መካከል አናደርገውም?
3. ተማሪዎች የልማት ሰራዊት ለመተግበር ስንሞክር ጎበዝ ተማሪዎች የራሴን ጊዜ ለሌላ ተማሪ አላካፍልም ቢለን ምን ዓይነት መፍትሄ አለን?
4. የልማት ሰራዊት ግንባታ ሲካሄድ ለምን ድጋፍ እና ክትትል ያንሳል?
አቶ ንጉሰም ልክ እንደ ዶ/ር አዲሰአለም ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ አልሰጡባቸውም፡፡ ይመስለኛል ፖሊቲክሊ ሰንስቲቭ የሆኑ እስዩስ መንካት አልፈለጉም፡፡ አንዳንዴም ሁለቱንም የዝግጅት እጥረት የነበረባቸው ይመስሉ ነበር፡፡ የሆነ ሁኖ አቶ ንጉሰ ከሰጥዋቸው ማብራርያዎች የሚከተሉትን መጥቀስ የቻላል፡፡
ቃሉ ምን ይሁን ምን ማትኮር ያለብን ስራው ላይ ነው፡፡ ሰራዊት የተባለበት ምክንያት ግን የለውጥ ሃይል በመገንባት ያለውን ስር የሰደደ ድህነት ተዋግተን ለሸነፍ የተጠቀምነው ስተራተጂ ለመግለፅ ነው፡፡ ሰራዊት ስንል ደግሞ ሰራዊት ዘርፈ ብዙ ሃላፊነት የሚሸከም እና ለሃገር እድገት በትጋት የሚሰራ ሐይል ሁሉ ለመግለፅ እንጂ ለወታደር ብቻ የሚሰጥ ስያሜ አይደለም፡፡
የልማት ሰራዊት ማለት ለለውጥ የሚተጋ ሐይል ነው ብለን ካልን አሁን ካለን መጠነ ሰፊ ድህነት የምንወጣበት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ እና ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮዎች ተወስዶ የተጠና መርህ በመሆኑ አሁን ባለው የሃገራችን የድህነት ማጥፋት ዘመቻ በተናጠል ከመስራት ይልቅ በብዱን እና በተደራጀ መልኩ መስራት ሁነኛ አማራች ነው፡፡
ተማሪዎች የግሌን ጊዜ ለሌላ ተማሪ አላካፍልም የሚል ጥያቄ ሊያነሱ የችላሉ፡፡ የኔትወርክ ዓላማ አንድ ተማሪ የሌላ ተማሪ እንዲሰራ ሳይሆን በጋራ መስራት፣ መደጋገፍ እንዳለባቸው ማሳመን እና ማስረዳት ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ሙሉ ጊዝያቸውን በጋራ መሆን አለበት ማለት ሳይሆን የጋራ ስራ በሚያስፈልግበት ጊዜ በጋራ የመስራት ልምድ እና ባህል እንዲዳብር ማድረግ ነው፡፡
One Response to በመቐለ ዩኒቨርስቲ ስልጠና ‘የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ እና አንድ ሃገራዊ የጋራ ማህበረሰብ መፍጠር’