አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 26፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዝው የሚስተዋሉ ችግሮችን ህወሃት እና ብአዴን በመነጋገር በጋራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈቱት የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደሩ ገለፁ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳሩ እና የህወሃት ሊቀመንበር አቶ አባይ ወልዱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ፥ የትግራይ እና አማራ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው፤ ትናንት ደርግን ለመጣል እና ዛሬ ደግሞ ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ የተዋጉ እና እየተዋጉ ያሉ ህዝቦች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑ የራሳቸውን አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ሁለቱን ህዝቦች ለመለያያት የያዙት አጀንዳ አይሳካም ብለዋል።
ክልሎቹ ከወሰን ጋር ያሉ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት በጋራም ይሰራሉ ነው ያሉት።
ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለክልሉ መንግስት የቀረበ ጥያቄ እንደሌለ በማንሳት፥ ከቀረበ ግን የክልሉ መንግስት እንደሚፈታው ርእሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።