Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በክልሉ አንዳንድ ከተሞች ህገ ወጥ ሰልፍ ለማካሄድ የሚሞክሩ ሃይሎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

image
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 29፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ህገ ወጥ ሰልፍ ለማካሄድ የሚሞክሩ ሃይሎች ከጥፋት ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስጠነቀቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት በህገወጥ መንገድ የሚካሄድ ሰልፍ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡

ሃላፊነቱን ወስዶ ፈቃድ የጠየቀም ሆነ የተሰጠው አካል እንደሌለ ያስታወቁት አቶ ገዱ፥ “የዜጎችን መብት ለማስከበርና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ የክልሉ መንግስት የተጣለበትን ሃላፊነት ይወጣል” ብለዋል።

በዚህም ህግና ስርዓትን ባልተከተለ መንገድ የሚካሄድ ህገ-ወጥ ሰልፍን ለማስቆም የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

“በዜጎች መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት በህገ ወጥ ሰልፍ ለማናጋት በሚጥሩ ሃይሎች ላይ በየደረጃው የሚገኘው የጸጥታ ሃይል አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ተሰጥቶቷል “ብለዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ የተካሄደውን ህገ ወጥ ሰልፍ የክልሉ መንግስት ለማስቆም የነበረውን አቅምና ዝግጅት ከህብረተሰቡ ጋር ቅራኔ ላለመግባት ሲባል መታለፉን ተናግረዋል።

ሰልፉ በዜጎች ህይወትም ሆነ ንብረት ጉዳት ባያደርስም የተላለፉ መልዕክቶች፣ ህጋዊነት የሌላቸው ባንዲራዎችና እንቅስቃሴዎች መቻቻልን፣ ህብረ-ብሔራዊነትንና ህገ-መንግታዊ ሥርዓቱን የተጻረሩ እንደነበሩ መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።

በዛሬው እለትም በጎንደር ከተማ ህገ ወጦች ህብረተሰብን በማነሳሳት የፈጠሩት የጎዳና ሁከት በአካባቢው ዳግም ብጥብጥና ሁከት እንዲከሰት አስችሏል።

አቶ ገዱ የክልሉ መንግስት በየጊዜው የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮችን በአዲሱ ዓመት በቁርጠኝነት ለመፍታት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በክልሉ በየትኛውም አካባቢና ቦታ ህገ-ወጥ በሆነ ሰልፍ ህብረተሰቡ እንዳይሳተፍ በመጠየቅ ይህን ለማስፈጸም የሚሯሯጡ ሃይሎችን ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ከጥፋት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አለበት ብለዋል።