የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ደግሞ የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች ውጤት አስገኝተዋል ብሏል።
ጽህፈት ቤቱ ዓለም አቀፉን የፕሬስ ነፃነት ቀን ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ የፓናል ውይይት አክብሯል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ዲን ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የፕሬስ ነፃነትን ከሃላፊነት ጋር አጣምረው የሚተገብሩ ተቋማት ሊፈጠሩ የግድ ይላል።
የመንግሥት ተቋማትም መረጃዎችን በመስጠት በኩል ያሉባቸውን ክፍተቶች መድፈን እንዳለባቸው ያመለከቱት ዶክተር ነገሪ የሚዲያ ባለሙያዎችን አቅም የመገንባቱን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የግል የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የፕሬስ ነፃነት አጠቃቀማቸውን መፈተሽ እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው በበኩላቸው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።
ተግባራቱ የመረጃ ነፃነት አጋዥ መሰረተ ልማቶችን መገንባት፣ የሰው ኃይሉን በክህሎትና በቴክኖሎጂ ማብቃትና የአሰራር ማዕቀፎችን ማሻሻልን ያካተቱ ናቸው።
ኢዜአ እንደዘገበው የፕሬስ ነፃንት በኢትዮጵያና የግንቦት 20 ትሩፋቶች፣ የመንግሥት ተቋማት መረጃ አሰጣጥና ማኅበራዊ ሚዲያውን የተመለከተ የመወያያ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በዓለም ለ25ኛ በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።