አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅርቡ የኤርትራ መንግስት አሰልጥኖ የላካቸው የሽብር ተላላኪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ በሀገር ውስጥ የዚህ ሀይል ተቀባይ እና ተባባሪን በመለየት በቁጥጥር ስር ለማዋል ባለመ መልኩ መከናወኑን እና ይህም በተሳካ ሁኔታ መፈፀሙን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የፀረ ሽብር የጋራ ግብረ ሃይል ገለፀ።
አንድ የግብረ ሀይሉ የስራ ሀላፊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮፖሬት እንደገለፁት ኦፕሬሽኑ የጥፋ ሀይሉን እንቅስቃሴ ከአስመራ ጀምሮ ከመከታተል ባለፈ ይህ ቡድን በአገር ውስጥ ያለውን ሰንሰለት ለመለየት እና በቁጥጥር ስር ለማዋል ታስቦ ተከናውኗል።
ወደ አገር ውስጥ የገባው ሀይል ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ሳይዝ መግባቱን ያነሱት ሀላፊው የዚህ ቡድን ተቀባይ ሀይሎች ግን ቀላል የጦር መሳሪያ እና ገጀራን የመሰሉ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን እንደታጠቁ መያዛቸውን ነው ያመለከቱት።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የሽብር ተላላኪዎች የሻዕብያ ተላላኪ የሆኑ እና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሀይሎች ተልዕኮን አስፈጻሚዎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
እነዚህን የሽብር ተላላኪዎች ቁጥር እና ዝርዝር ማንነታቸውን በተመለከተ ወደፊት ከምርመራ በል ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ነው የገለፁት።
የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች ስማቸውን በመቀየር የኤርትራ የጉዞ ሰነድ ከተዘጋጀላቸው በኋላ ከአስመራ ተነስተው ወደ ኡጋንዳ በአውሮፕላን ቀጥሎም በተሽከርካሪ ወደ ኬኒያ ተጉዘው በሞያሌ በኩል ድንበር ተሻግረው በደቡብ ክልል በሚገኝ ጫካ ውስጥ ያልታወቁ መስሏቸው ራሳቸውን በመደበቅ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ ሃይሉ መግለፁ ይታወሳል።
በዚያም ለተለያዩ የሽብር ተግባራት ሲዘጋጁ ግብረሃይሉ ባካሄደው ኦፕሬሽን ሚያዚያ 28 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት በቁጥጥር ስር ውለዋል። በወቅቱ ለማምለጥ የሞከሩ ጥቂት አሸባሪዎችም ተገድለዋል።