በጋምቤላ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበሩ 10 ኢትዮጵያዊያን ህልፈት የተጠረጠሩ 30 የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
በጃዊ የስደተኞች መጠለያ ላይ የደረሰ የመኪና አደጋን ምክንያት በማድረግ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ለ10 ኢትዮጵያዊያን ህይወት ማለፍ ምክንያት እንደሆኑ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር አስታውቀዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጋትሏክ ቱት ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ንብረትነቱ የህፃናት አድን ድርጅት /ሴቭ ዘ ችልድረን/ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሆነ አንድ ተሽከርካሪ በስደተኞቹ ካምፕ ባደረሰው አደጋ ሁለት የስድተኞች ልጆች መሞታቸውን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ ጥቃቱን በኢትዮጵያዊያኑ ላይ የፈፀሙት። ጥቃት አድራሽ ስደተኞቹ በጃዊ የስደተኞች መጠለያ ይሰሩ በነበሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ሚያዝያ 13፣2008 ባደረሱት ጥቃት የ10 ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ማለፉን ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የተናገሩት።
በመጠለያው የደረሰው የመኪና አደጋ በማንኛው ሁኔታና በየትኛውም ቦታ ሊከሰት የሚችል መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ የኢትዮጵያ መግንሥት ከአገራቸው ተሰድደው ለመጡት የደቡብ ሱዳናዊያን ሰብዓዊ ድጋፍና እንክብካቤ እያደረገ ባለበት ሁኔታ ከመኪና አደጋው ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ይህን ሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበሩ ኢትዮጵያዊን ላይ በደረሰው ጥቃት በክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አደጋውን እንዳደረሱት የተጠረጠሩ 30 ስደተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘና ሰሞኑን በተፈጠረው ጥቃት በአካባቢው የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስና የክልሉን ሰላም ለማጠናከር የአካባቢው አስተዳደር ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በጥብቅ ተሳስሮ እየሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ መግለፃቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ዘግቧል፡፡