ዙና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ዘሪሁን ጌታሰው፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ለማቅረብና ከተለያዩ የንግድ ሥራ ውሎች የሰበሰቡትን ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ይዘው መሰወራቸው ተሰማ፡፡
አቶ ዘሪሁን የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽኖች፣ ሲኖትራኮችና አውቶሞቢሎችን ከ60 እስከ 75 ቀናት ድረስ ወደ አገር ውስጥ አስገብተው እንደሚያስረክቡ ከደንበኞች ጋር ተዋውለው ነበር፡፡ ውሉ ይህን ቢልም፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በተላለፈ ማስታወቂያ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚያስረክቡ አስታውቀው ነበር፡፡
ነገር ግን የአቶ ዘሪሁን ኩባንያ ዙና ትሬዲንግ በገባው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተሽከርካሪዎቹንና ማሽኖቹን ባለመስረከቡ ክፍያ የፈጸሙ ግለሰቦችን ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡
ከደንበኞች ጫና በመብዛቱ አቶ ዘሪሁን ሲኖትራኮችንና ማሽኖችን ለማምጣት ወደ ውጭ መሄዳቸው በኩባንያቸው ሠራተኞች እንዲገለጽ ተደርጎ፣ መጋቢት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ አስነግረው ነበር፡፡ ነገር ግን ከኢምግሬሽን በተገኘው መረጃ መሠረት አቶ ዘርይሁን ባለፉት አሥር ቀናት በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከአገር አለመውጣታቸው ተሰምቷል፡፡
ይህም ሆኖ አቶ ዘሪሁን በተጠቀሰው ቀን ወደ አገር ቤት ባለመመለሳቸው ተስፋ የቆረጡ ከ60 በላይ ደንበኞች ተሰብስበው ለፖሊስ አመልክተዋል፡፡ በወቅቱ በኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጎዳና ከትራፊክ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ጎላጉል ሕንፃ አምስተኛና ዘጠነኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የዙና ትሬዲንግ ቢሮ የተሰበሰቡ ደንበኞች፣ ቢሮው ዝግ በመሆኑ የኩባንያው ሠራተኞች አለመኖራቸው ያስደነገጣቸው ከመሆኑም በላይ ገንዘባቸው አልባሌ ቦታ መውደቁን በመቁጠር በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ወድቀው ታይተዋል፡፡
የኩባንያው ደንበኞች አድራሻ በመለዋወጥ ወኪሎቻቸውን ከመምረጣቸውም በተጨማሪ ለአዲስ አበባ ፖሊስ አመልክተዋል፡፡ ጉዳዩን የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ የያዙት ሲሆን፣ ዓርብ መጋቢት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌዴራል ፖሊስ አቶ ዘሪሁንን አድኖ ወደ አገር ለማምጣት ለኢንተርፖል ደብዳቤ መጻፉ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የዜጎችን ገንዘብ ሰብስቦ ችግር ውስጥ ጥሎ የሚኮበልል ማንኛውንም ሰው ወደ አገር ቤት አምጥቶ ለፍርድ እንደሚያቀርብ ለደንበኞች ቃል እንደገባላቸው ተጠቁሟል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ ከዙና ትሬዲንግ ሲኖትራኮችንና የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ለመግዛት ከ170 በላይ ሰዎች ውል ገብተው እስከ 50 በመቶ ክፍያ መፈጸማቸው ታውቋል፡፡ የተወሰኑት ውሉ ፈርሶ ገንዘባቸው የተመለሰላቸው አሉ፡፡ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ውሎች በርካታ ገንዘብ በአቶ ዘሪሁን መሰብሰቡ ታውቋል፡፡ 150 ያህል ደንበኞች ከ300 ሺሕ ብር እስከ 750 ሺሕ ብር ድረስ ለኩባንያው መክፈላቸው ይነገራል፡፡
አንድ ሲኖትራክ ጠቅላላ የመሸጫ ዋጋው 1.4 ሚሊዮን ብር በመሆኑ አብዛኛዎቹ ደንበኞች 50 በመቶ ክፍያ መፈጸማቸው ተሰምቷል፡፡
የዙና ትሬዲንግ ድረ ገጽ እንደሚያብራራው ኩባንያው በሦስት ዋና ዋና የሥራ መስኮች ተሰማርቷል፡፡ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ማለትም ቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ ይልካል፡፡ ለገጣፎ አካባቢ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማራ መሆኑና የኮንስትራክሽን ማሽኖችንና አውቶሞቢሎችን እንደሚያስመጣ ድረ ገጹ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም አሸዋና ሲሚንቶ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲያቀርብ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከቃሊቲ ጉምሩክ ጀርባ ወርቁ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጉምሩክ መጋዘን በ2,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንዳለው ተገልጿል፡፡
የዙና ትሬዲንግ ኩባንያ ባለቤት በመሰወራቸው ገንዘብ የከፈሉ ደንበኞች የኩባንያውንና የአቶ ዘሪሁንን የባንክ አካውንቶች፣ እንዲሁም ንብረቶች ለማሳገድ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ዘሪሁን በድርጅቱ ባንክ አካውንት ውስጥ ምንም ሳያስተርፉ ይዘው ከመሰወራቸውም በላይ፣ ባለቤታቸውና አብሯቸው ይሠራ የነበረ ወንድማቸው የት እንደደረሱ አልታወቀም፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞችም አቶ ዘሪሁን ቃል በገቡት መሠረት ባለመመለሳቸው ደንበኞችን ፍራቻ ሥራ ማቆማቸው ታውቋል፡፡Source :Reporter