መጋቢት 13 ፣2008
የዙና ትሬዲንግ 5 ሠራተኞችን የአዲስ አበባ ፖለሲ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር አዋለ።
በቁጥጥር ስር ከዋሉ 5ቱ ሠራተኞች መካከል አንዱ የድርጅቱ ማርኬቲንግ ስራ አስኪያጅ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ለኢቢሲ የገለፀው፡፡
በኮሚሽኑ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዥንን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሻምበል ሙሉ ሰው እንዳሉት ከማናጀሩ ውጪ ያሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች የድርጅቱ የሂሳብ ሠራተኞች ናቸው፡፡
ከሁለት ቀናት በፊት ኮሚሽኑ በድርጅቱ ተጭበረበርን ያሉ አመልካቶች ቁጥራቸው 51 የነበረ መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን ዛሬ ላይ ቁጥራቸው ከእጥፍ በላይ ደርሷል፡፡
እንደ ምክትል ኮማንደሩ ገለፃ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዘሪሁን ጌታ ሰው ወልደአረጋይን የመፈለጉን ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ዙና ትሬዲንግ ገልባጭ ተሽከርካሪዎችን አስመጣላችኋለሁ በማለት ከበርካታ ሰዎች ከ6መቶ እስከ 7መቶ ሃምሳ ሺ ብር በመቀበል በመሰወሩ በርካቶች ቅሬታ ማቅረባቸውን ጣቢያችን መዘገቡ አይዘነጋም፡፡