አዲስ አበባ ጥር 28/2008 የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የቴክኖሎጂ አቅሙን በማጠናከር ለአፍሪካዊያን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መስራት ይገባዋል ሲሉ የቦርድ ሰብሳቢው ተናገሩ።
የኮርፖሬሽኑን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ አስመልክቶም በዛሬው እለት ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ኃላፊ ሚኒስትርና የኢብኮ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ረዳ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ አፍሪካዊያንን ለማገልገል መስራት ይገባዋል።
አሁን ያለውን 86 በመቶ የአገር ውስጥ የስርጭት አድማስ መቶ በመቶ ማድረስ እንዳለበትም እንዲሁ።
ኢብኮ የኢትዮጵያ ሕዳሴ እንዲፋጠን በማድረግ እስካሁን ያበረከተውን አስተዋጾ አድንቀው በቀጣይም የብዝሃነትና የህዳሴ ድምፅነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
“ተቋሙ በራሱ ገቢ የሚተዳደር በመሆኑ የየትኛውም አካል ጣልቃ ገብነት ሳይኖር የጀመራቸው ዘመናዊ አስተሳሰብና አስራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቅርቡ የጀመረውን የአስራር ማሻሸያና የለውጥ ሂደት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፓናሊስቶች ገለጹ።
የኮርፖሬሽኑን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ አስመልክቶ ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን ባለፉት ሁለት አመታት በከፍተኛ መሻሻል ውስጥ መሆኑ ተነስቷል።
ይህንኑ የለውጥ ሂደትና የአስራር ማሻሻያ ይበልጥ ለማጠናከር ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዳለበት ተጠቁሟል።
ከአገሪቱ አልፎ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱ ተጠቃሽ ለመሆን መስራት እንዳለበትም እንዲሁ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃነ ኪዳነማሪያም በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የተለያዩ ለውጦችን በማድረግ አዲስ አቀራረብ ይዞ ለመምጣት ጥረት ይደረጋል።
በአሁኑ ወቅት የቢዝነስ ፕላን መንደፉን ጠቁመው በመጪው ሰኔ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
ለዚህም ተግባራዊነት ሌሎች የሚዲያ ተቋማትና አጋሮች ከኮርፖሬሽኑ ጎን እንዲቆሙና ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የቀድሞው ኢቲቪ የአሁኑ ኢቢሲ የዛሬ 50 ዓመት ስርጭቱን ሲጀምር በ40 ደቂቃ የአየር ሰዓት ሲሆን በአህኑ ወቅት የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።