አገራዊውን የከተማ መሬት ይዞታ መብት ምዝገባ ሥርዓት በዘመናዊ መረጃ በመገንባት ስር የሰደደውን የመሬት አስተዳደር ችግር መፍታት እንደሚቻል የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትና የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲዎች በከተማ መሬት ይዞታ መብት ምዝገባ ሥርዓት የሲስተም ልማት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሚንስትር መኩሪያ ኃይሌ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት አገሪቱ የጀመረችውን የዴሞክራሲ ግንባታና ፈጣን የልማት ዕድገት ለማስቀጠል በከተሞች የሚታየውን የመሬት አስተዳደር ችግር በዘላቂነት መፍታት ይገባል።
የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ እንደገለጹት የመሬት አስተዳደርን በዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት በመገንባት ግልፅነት መፍጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ፣ የደረጃና የአሰራር መመሪያ ሲዘጋጅ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም ሂደቱ ተጠናቆ ሥርዓቱን መተግበር የሚያስችል የሲስተም ልማት ምዕራፍ ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ወደ ተግባር ለመግባትም የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሥርዓት ልማት በግንባታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የሚለማው ሲስተም የአገሪቱን የህግ ማዕቀፎች መሰረት ያደረገና የዜጎችን የመሬት ይዞታ የመጠቀም መብት አስተማማኝ ማድረግ የሚያስችል እንዲሆን ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።
የሲስተም ልማቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግም አይጅን የተባለ ዓለም ዓቀፍ የፈረንሳይ ኩባንያ በአማካሪነት መቀጠሩን ጠቅሰዋል።
ሥርዓቱ ከተሞች መሬታቸውን ቆጥረው እንዲያስተዳድሩ ስለሚያደርግ በዘርፉ የሚታየውን ኪራይ ሰብሳቢነት በማስወገድ ዜጎች ምን ያህል መሬት በማን እጅ እንደሚገኝና ለምን አገልግሎት እንደዋለ የሚያውቁበት ሁኔታ የሚፈጥርም ነው ተብሏል ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ፕሮጀክቱ በ22 ወራት እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።
ኤጀንሲው የመሬት ይዞታን ማስመዝገብ፣ ማረጋገጥ፣ መሰረዝና ማስተላለፍን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ የማምረትና የማበልፀግ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ወደ ክልል ከተሞች እንዲሁም በአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ መብት ምዝገባ አገልግሎት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በመቀጠል በ23 የክልል ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።
One Response to የመሬት ይዞታ ምዝገባን በዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈፀመ