በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የክልሉን መንግስት አቋምን በሚተነትነው ፅሁፍ ላይ እንደተገለፀው በክልላችን የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ማረሚያ ቤቶችን በመስበር፤ የህግ ታራሚዎችን የመልቀቅ፣ የፖሊስ ጽህፈት ቤቶችን፣ የልማት ድርጅቶችን፤ የአርሶ አደር ምርቶችን፤ የግል መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠልና በማውደም በጦር መሳሪያ በመታገዝ የጥፋት ተግባራቸውን በመፈፀም ላይ ያሉ ፀረ ሰላም ሃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
እነዚህ ፀረ ሰላም ሃይሎች አብሮ የመኖር፤ መቻቻልና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ተምሳሌት የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ወንድሞቹ ጋር የጎሪጥ እንዲተያይ፤ እንዲሁም በእምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከድርጊታቸው ጎን የቆመን ሀይል ሁሉ አሰልፈው ወደ ህገ ወጥ ተግባር ተሸጋግረዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የእነዚህን የጥፋት ሀይሎች ያልተገባ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱን የመናድ ተግባር ለማስቆምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በህገመንግስቱ የተጣለበትን ግዴታ መሰረት በማድረግ በድርጊቱ ዋና ተዋናዮች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡