Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ/Amharic Version/

የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23-25/2012 ዓ.ም በክልላችንና በሃገራችን እንዲሁም በንኡስ ቀጣናው የተከሰቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት በመመርመር የውሳኔ ሃሳቦችን አሳልፏል፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክልላችን እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የክልላችንና የህዝባችን ድህንነት የመታደግ ሥራዎችን እንዲሁም የኮረናን ወረርሽኝ ለመመከት የተሰሩ ሥራዎች በሚመለከት በዝርዝር የተወያየበት ሲሆን፣ እስካሁን የታዩ ጥንካሬዎችን ጠብቆ ለማቆየትና የታዩ ጉድለቶችን ለማረም የተሰሩ ስራዎችን በመመርመር ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በክልላችን ያሉ ወይም የሚኖሩ ፈተናዎች ለመመከት አሁንም ወሳኙ ውስጣዊ ጥንካሬያችን መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ በዚህ ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሦስት ቀን ስብሰባው በስፋት ከመከረባቸው ጉዳዮች ዋነኛው በሃገር ደረጃ በብልፅግና እየተካሄደ መጥቶ አሁን በመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት የመናድ ዘመቻ የሚመለከተው አጀንዳ የጎላ ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዝርዝር ተወያይቶ እንዳስቀመጠው ብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት ያላሳየበትን ሃገራዊ ምርጫ የCovid 19 ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ-መንግስታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ እንደታየው የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመቀበል በሚል በተጠራ የይስሙላ መድረክ ላይ ጠ/ሚ/ሩ ያለቀለት ያሉትን ሃሳብ ማጠናቀቂያ ክፍል ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ አመላክተዋል፡፡

የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህ ያለ በቂ ዝግጅትም ሆነ ያለ ግልፅ አጀንዳ የተጠራውና ጠ/ሚ/ሩ ከህግ ውጭ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት መድረክ ተከትሎ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግናን ህገወጥ የስልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ አስምሮበታል፡፡ አሁንም ሥልጣን ላይ ባለው ኣካል የተጀመረውና ሕገ-መንግስትን መተርጎም በሚል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ግልፅ ሆኗል፡፡

በዚህም መሰረት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

1. የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግስቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የተጀመረው ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም፡፡ ሕገ-መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሰረት አሻሚ ሁኖ ለተገኙ አንቀፆች እንጂ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ይህንን ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፍያ በአስቸኳይ ቆሞ አሁንም የኮረናን ወረርሽኝ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ ሃገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውሰጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ ሃገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል፡፡

2. ብልጽግና የንደዚህ ዓይነቱ መድረክ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ነፃና ግልፅ ምርጫ የመምራት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ብቃት የሌለው በመሆኑ ይህንን ለማስፈፀም የሚችል የተለየ አደረጃጀት የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሦ የሃገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስከበር አስፈላጊነት በቂ ትኩረት በሰጠ መልኩ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲጀመር ጥሪውን ያቀርባል፡፡

3. ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወትሮውኑም ገዢውን ፓርቲ በሕገ ወጥ መንገድ አፍርሶ ራሱን በወራሽነት ያስቀመጠው ብልፅግና ከመስከረም 25 ቡኃላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ጠባብም ቢሆን ዕድል የማይኖር በመሆኑ የሀገሪቱ ችግር ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት ዕድል መፈጠሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ ህወሓት እንደዚሁ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ ሃገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የትግራይ ህዝብ በመስዋእትነቱ በተከለው ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት አይፈቅድም፡፡ ለዚህም ሲባል ከትግራይ ህዝብና ለትግራይ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ እውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የህዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስኗል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የፀረ ኮረና ዘመቻችንን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ህገ-መንግስታዊ መርሆዎችን ባሟላ መልኩ የሚፈፀም ይሆናል፡፡

4. የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌደሬሽን ምክርቤት አባላት ህልውናቸው ያረጋገጠውን ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሃይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያርቁ በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

5. በመጨረሻም ህወሓት ሆነ የትግራይ ህዝብ የሕገ-መንግስታዊ ሥርዓታችን ያረጋገጠውን ሕብረብሄራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማዳን በሚደረገው ርብርብ መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሄር ብሄረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡

የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጽ/ቤት
26/08/2012 ዓ.ም