Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ብርቱካን ሚደቅሳ ለምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢነት? —— ከገ/ኣ

ጠ/ሚር ኣብይ ኣህመድ ብርቱካን ሚደቅሳን የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሆነው እንዲሾሙ ባቀረቡት መሰረት በዕለቱ ከ200 በላይ የምክር ቤቱ ኣባላት ባልተገኙበት የተወካዮች ምክርቤት ሹመቱን ኣፅድቆላቸዋል። የተሿሚዋ ገለልተኝነትና የውጭ ዜግነት ስለመያዛቸውን ኣስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱ ግለ ሰብዋ የማንም የፖለቲካ ድርጅት ኣባል እንዳልሆኑ እና በናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ በሚባል ድርጅት በተመራማሪነት ይሰሩ እንደነበር ኣብራርቷል። የውጭ ዜግነትን ኣስመልክቶ ግን ግልፅ የሆነ መልስ ኣልሰጡም። በነገራችን ላይ ዶ/ር ብርሃኑ፣ ብዙ የግንቦት ሰባት ኣርበኞች ኣባላት እና ነባር የኦነግ ኣባላት የውጭ ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ ይታወቃል።

ሌላው እንደተባለው ይሁን ብለን እንውሰድና ግለ ስብዋ የናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ ሰራተኛ መሆናቸውን ብቻ ከባድ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ይህ ድርጅት በተለመደው የምዕራባዊያኑ ቅጥፈት የግል ወይም ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት ለመምሰል ቢሞክርም ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እና ድሃ ኣገሮችን ክሚዘርፉ ካፒታሊስቶች ገንዘብ በማሰባሰብ በባለቤትነት የሚመራው ታዋቂው የኣሜሪካን ዴምክራቶች ፓርቲ ነው። ዋና ስራውም በኣለም ዙሪያ ዴሞክራሲ እናስፋፋለን በማለት ሲቻል በዘዴ ሳይቻል በቀለም ኣብዮት መንግስታትን እየቀያየረ የኣሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ታዛዥ መሪዎችን ወደ ስልጣን ማብቃት ነው። ይህ ድርጅት ሰዎችን በጥንቃቄ በመመልመል እና የትምህርት እና የስራ ዕድል በማመቻቸት የኣሜሪካ ኢንተረስት ሊያስፈፅሙ የሚችሉ ፖለቲከኞች፣ ኣክቲቪስቶችን እና ጋዜጠኛ ነን ባዮች ኣሜሪካን ድረስ ወስዶ ያሰለጥናል፣ ባሉበትም ፋይናንስ ያደርጋል።

ቀደም ሲል በነበሩት ኣመታትም እነ ብርቱኳን ሚደቅሳ የነበሩበትን የቅንጅት ፓርቲ ስብስብ ወደ ስልጣን ለማምጣት በተደረገው ሙከራ የኣሜሪካ እና የኣውሮፓ መንግስታት ሴራ ምን ያህል ኣጥፊ እና ኣገራችንን ከባድ ፈተና ላይ የከተተ እንደነበር ሁሉም የሚያስታውሰው ነው። የታሰበውን ሳይሆን ሲቀር ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ የተባለው ድርጅት ብርቱኳን ሚደቅሳን ስኮላርሺፕ ሰጥቶ በኣሜሪካን ምድር ሲያሰለጥን የነበረ እና ኣሁንም ከኣሁን ቀደም ማሳካት የቸገረውን የጥቅም ፖለቲካ በተሟላ መልኩ ያስካ ዘንድ ግለሰብዋ በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት እንድትሾምና የኣብይ ኣህመድ ኣጋር ሆና የኣሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር የፖለቲካ ሃይል ወደ ስልጣን ለማብቃት እንዲያስችል የተዘየደ ዘዴ መሆኑን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው ይገባል።

እንደሚታወቀው ሃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣኑን ሊለቅ እና እነ ኣብይ ኣህመድ ወደ ስልጣን ሊመጡ የኣሜሪካ መንግስት ሚና ከፍተኛ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ኣሁንም በየቀኑ የሚሄዱበት ኣቅጣጫ እና የሚከተሉትን የፖለቲካ መስመርን ኣስመልክቶ ምክር በማስመሰል መመሪያ በኣሜሪካን ኤምባሲ በኩል እንደሚቀርብላቸው የታወቀ ነው። ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በኃላ የፖሊሲ ነፃነት ይቅርና የኣገር ሉኣላዊነትዋን የጠበቀች ኣገር ኣለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ እውነትም ተኝቷዋል ኣሊያም ደንዝዘዋል።

ብስልጣን ብቻ ከመታወራችን በላይ የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያታዊነትና ሚዛናዊነታችንን ኣስቶ ነፃነቱን ጠብቆ የኖረውን ህዝብ እና ኣገር እንደ ሌሎቹ የኣፍሪካ ኣገሮች በየእጅ ኣዙር ቅኝ ግዛት እያስገባን እንደሆነ ጥርጥር የለም። ኣገሪቱ በእነዚህና በመሳሰሉት ለህዝባቸው ሳይሆን ለውጭ ሃይሎች ያደሩ ፖለቲከኞች መዳፍ ላይ ወድቃ ለ27 ኣመታት የተዘመረለት ፈጣንና ኣገር በቀል የኢኮኖሚ እድገት በኣለም ኣቀፍ ተቋማት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ድምጥማጡን ጠፍቶ የኣለም መሳለቂያ የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ ኣይደለም። ያኔ ቁጭት ኣይመልሰውም። የሰላሙን ነገርማ ሆድ ይፍጀው ሳይሆን ኣዲዮስ ኢትዮጵያ የሚያስብል ሆነዋል።

ለማነኛውም ተሿሚዋ የሚመሩትን የምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ኣገራዊ ምርጫ ከበፊቱ ባልተናነሰ ኣወዘጋቢ እንደሚሆን ከወዲሁ መተንበይ ይቻላል። በኣንድ ወገን በውስጥ የፖለቲካ ሃይሎች ንትርክ እና የማይታረቅ ፍላጎት በሌላ ወገን ደግሞ የተለመደው የውጭ መንግስታት ጣልቃ ገብነት ተወጥሮ ኣገሪቱን የከፋ ኣደጋ ላይ ልትደርስ ትችላለች የሚል ግምት ኣለ።

ቸር ያሰማን

ገ/ኣ ነኝ