Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የጎራ መደበላልቅ፣ የኢህኣዴግ እጣ ፈንታ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ኣዲስ ኣሰላለፍ ስናስብ :ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ ነሃሴ 2010 ዓ/ም

በኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ውስጣዊ ክፍፍል መፈጠሩን ግልፅ ከሆነ ቆየ። ሃ/መሪያም ደሳለኝ እንዳሉት የቀድሞው ጠ/ሚንስትር ኣቶ መለስ ዜናዊ መሰዋት ተከትሎ ብኣዴን እና ኦህዴድ የስልጣን ሽሚያ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል። ሃሳባቸው ይሳካ ዘንድም ሁለቱም ኣንድ ኣይነት መንገድ መከተል መረጡ። በኣንድ በኩል ኣንዱ ኣንደኛውን ተጠቅሞ የጠ/ሚንስትርነት ስልጣን መቆናጠጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ የበላይነት በሚል መሰረተ ቢስ አና ኣደገኛ መርዝ በመርጨት ኣገር ኣቀፍ የፖለቲካ ቀውስና ያለመረጋጋት ፈጥሮ ህወሓት ላይ ተፅእኖ መፍጠር ብሎም ከጨዋታ ውጭ ማድረግ ነው። ኣንደኛውም መንገድ በውስጣዊ መቧደን ብቻ የሚፈጸም ሲሆን ሁለተኛው ግን ኢህኣዴግ የሚከተለውን ሪኣተ ዓለም እና ድርጅታዊ ኣሰራርን በመጣስ ኢህኣዴግን ኣምርረው ከሚጠሉና ከሚቃወሙ ሃይሎች ጋር (የደርግ ትርፍራፊ እና ሻዕቢያም ጭምር) መሰለፍን ይጨምራል። ይህንን ቀውስ እንደ መልካም ኣጋጣሚ የተመለከቱ የውጭ ሃይሎችም እነሱ ከሚከተሉት ሪዖተ ዓለም በተፃራሪ የልማታዊ መንግስት ኣስተሳሰብ በመከተል የኣገሪቱን ሉኣላዊነት ኣስከብሮ በተጎናፀፈው ሁለንተናዊ እድገት ለሌሎች ኣፍሪካ ሃገሮችም የሚጠቀስ ኣርኣያ ሆኖ የቆየውን የኢህኣዴግ መንግስት ለማፍረስ ይቻል ዘንድ ሁሉም ኣይነት ድጋፍ የመስጠት ሚና የተጫወቱ ሲሆን ኣሁንም የመንግስትን የውስጥና የውጭ ፖሊሲ ኣቅጣጫ ተቋሚ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።

በዚህ ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ኣመታት እጅግ ኣስገራሚ የሆኑ የጎራ መደበላለቅ ታይቷል፣ ኣሁንም ቀጥሏል። በተለይም ብኣዴን ከኢህኣዴግ ጎዳና ወጥቶ ኣዳዲስ እና ነባር በኢትዮጵያ ኣንድነት ስም ሲነግዱ የነበሩ የደርጉ ስርኣት ትርፍራፊና ጠባብ የኣማራ ብሄርተኞች በማሰባስብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ድምር ጡንቻውን ለማሳየት የሚሞክርበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ የሆነውም በኣገሪቱ የመቻቻል ፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ ስርኣትን ከመገንባት ካለው ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን በኣንድ በኩል እንደ ታሪካዊ ጠላት የፈረጀው ህወሓትን ለማፋለም ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኣሁን እየታየ ያለውን የኦህዴድ እና ብዛት ያላቸው የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች የመሰባሰብ ሁኔታ ስጋት ላይ ስለጣላቸው ብቻ እንደሆነ ለማንም ግልፅ መሆን ኣለበት። ኦህዴድም በኣንድ በኩል የኣብይ ኣህመድ የግል ፍላጎት በሚመስል የደርግ ስርኣት ሹማምንቶችና ጀሌዎቻቸውን እስከመወዳጀት የሄደና የተውገረገረ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ (ኦህዴድ) ኣቅጣጫው የማይታወቅ እና መርህ ኣልባ ፖለቲካ እያራመደ እንደሆነ ግልፅ ነው።

እንቅስቃሲያቸው ሁሉ ስልጣንን ማእከል ያደርገ እንጂ የሚከተሉት ሪኦተ ዓለም ወይም እንታገልለታለን ከሚሉት የፖለቲካ ፕሮግራምና ህዝብ ጋር ኣንዳች ግኑኝነት የለውም። ለምሳሌ፣ ኣሁን ያለው የፌደራል ስርኣት እየደገፈ ከመጣው ኦህዴድ ከመደገፍ ወደ መቃወም ከተሸጋገረው ብኣዴን እና በዙሪያው ከተሰለፉ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ጋር መወዳጀት የታየበት ሁኔታ እያየን ነው። ሁሉም ግን መርህ ኣልባ ናቸው። ኣንዱ ኣንደኛውን የሚፈልገው ኣራት ኪሎ ቤተመንግስት እስኪደርስ ድረስ ብቻ ነው። የቅንጅት ጊዜ እንደምናስታውሰው ‘’ቤተመንግስት ለመግባት ኣንድ ኪሎ ሜትር ቀረን’’ ባሉበትና ስልጣን የመያዝ ተስፋቸው እጅግ ከፍ ባለበት ሰኣት በውስጥ ሹኩቻ መበታተናቸው ልብ ይለዋል።
የሆነ ሆኖ የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች የተከተሉትን የጎራ መደበላልቅ አና መርህ ኣልባ ግኑኝነት ኣንዳንዶቹን ጊዚያዊ ድል ኣጎናፅፈዋቸው ሊሆን ቢችልም ኣሁንም ኣራቱ ድርጅቶች የያዘው ኢህኣዴግ ኣገር እየመራ ነው። ውሎ ኣድሮ ሁሉም የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች እስከ ኣሁን የሄዱበት መንገድ እና በየጎራቸው የፈጠሩትን መርህ ኣልባ ግኑኝነት ያልተጠበቀ ውጤት ኣስከትሎ ኣዲስ ኣሰላለፍና ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ትርምሱ ይቀጥላል። ኣሁን ባለው ሁኔታ ረጅም ርቀት እንደማይሄድ ከወዲሁ በርካታ ምልክቶች እያየን ነው። በትክክል ለመተንበይ በሚያስቸግር የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ሆነንም ቢሆን የኢህኣዴግ ቀጣይ ጉዞ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ኣይከብድም።

ተስፋ የሚደረገውና መሆን ያለበት ሁሉም የኢህኣዴግ ድርጅቶች ቆም ብለው ራሳቸውን ከኣባል ድርጅቶች ጋር ማወዳደርን ትተው ውስጣዊ የፖለቲካ ኣቋማቸውን ቢፈተሹና የዓላማ ኣንድነት እና መርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ህብረትና ኣቅጣጫ ቢከተሉ ለኣገርም ሆነ ቆመንለታል ለሚሉት ህዝብ እንደሚጠቅም ኣጠያያቂ ኣይሆንም። አዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ኣባል ድርጅቶቹ ሲከተሉት ከነበሩት የኢህኣዴግ የጋራ የፖለቲካ ፕሮግራም ውጭ ለመሄድ ከፈለጉም እንደ ከህደት ሳይሆን እንደ መብታቸው መታየት ይኖርበታል። ሲጀምር በሁሉም ነገር መቶ ለመቶ ተስማምተው ኣልነበረም ግንባር የፈጠሩት። ሲቀጥል ጊዜ የሚወልዳቸው ኣዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ኣመለካከትና ስልት የመቀየር ፍላጎትች ልዩነት እንደሚፈጠሩ ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል። የፖለቲካ ኣቅጣጫ ለመቀየር ግን በሌሎች፣ ያውም ኣብሮህ በኣንድ ፕሮግራም ጥላ ስር አየታገለ ባለው ድርጅትና እሱ በሚመራው ህዝብ ላይ የፖለቲካ ሴራ መጎንጎን እና ዘረኝነት እንደ መሳሪያ መጠቀም የግድ ኣይልም። ለሁሉም ኣይጠቅምና።

እንግዲህ የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች እንደምናውቀው የፌደራል ስርኣት ኣራማጆች ነበሩ። ኣሁን በተፈጠረው ሁኔታ ግን ከዚህ ኣስተሳሰብ ያፈነገጡ ድርጅቶች እንዳሉ ግልፅ ነው። ለምሳሌ ብኣዴን ሙሉ በሙሉ ወጥቶ ኣዲስ መንገድ እየተከተለ ነው። ባለፉት ኣመታት በኣማራ ክልል ተቀባይነት እንዳያገኝ ያለ የሌለ የፕሮፓጋንዳ ሃይላቸውን ተጠቅመው ሲታገሉት የነበሩ ፅንፍ የረገጡ ሃይሎች ጋር መወዳጀት መርጠዋል። በቀና መንገድ ታግሎ የህዝብ ድጋፍ ከማግኘት ይልቅ ኢህኣዴግ ያለፈውን ስርኣት ተፋልሞ በመገርሰስ፣ ብኣዴንን በማጠናከር፣ ኢህኣዴግ በመመስረት እና ኣዲስ ህገ-መንግስታዊ ስርኣትን በመመስረት ወሳኝ ሚና ከተጫወተው ህወሓት ጋር በመጣላት ከምድረ ገፅ ሊያጠፉት ሲታገሉት ከነበሩ የቂም ሃይሎች ጋር መሰለፍ የቀለለ ሆኖ ኣግኝቶታል። በቅርቡ ባወጣው የድርጅቱ መግለጫም ቀጣይ ኣቅጣጫው ግልፅ ኣድርገዋል። ብኣዴን የፌደራል ስርኣቱን፣ ህገመንግስቱን እና ክልሎችን ኣፍርሶ ከእንደገና እስከ ማዋቀር የሚዘልቅ ፍላጎት እንዳለው አቅርቡ ባወጣው መግለጫ ግልፅ ኣድርገዋል።

ኦህዴድ እስከ ኣሁን የቆየውን የፌደራል ስረኣት አንደሚያንስበትና ኣሁን ካለበት በላይ የጠነከረ እውነተኛ የፌደራል ስርኣት ማየት እንደሚፈልግ ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም የድርጅቱ ሊቀመምበር ኣብይ ኣህመድ እና ጥቂት ኢትዮጵያን ከገዛን ላይቀር የሚል እሳቤ ያስጎመጃቸው የኣማአራር ኣባላት እየተከተሉት ያሉት መንገድ ግን የዚሁ ተቃራኒ ነው። እንዲያውም ኣካሄዱ ብኣዴን እና በዚሁ ጎራ ከተሰለፉት የኣንድነት ሃይሎች ጋር የቀረበ ነው። በመሆኑም ኦህዴድ ያለው ኣማራጭ ሊቀመምበሩና ጥቂት ኣመራሮች እየተከተሉት ያሉት የፖለቲካ ኣቅጣጫ መጓዝ እና ፍፃሜውን ማየት ወይ ቀደም ሲል ሲታገልለት የቆየውን ፌደራሊስት ኣስተሳሰብ ይዞ መሄድ ነው። ኦህዴድ የፊተኛው ከመረጠ ብዙ ርቀት ሳይሄድ እንደ ጉም መትነኑ የማይቀር ሲሆን የኋላኛው ከመረጠ ግን ከበድ ያለ ውስጣዊ ትግል የሚጠይቀው ቢሆንም በኣንዱም ወይም በሌላ ኣደረጃጀት ቀጣይነቱን ያረጋግጣል። ይህ ግን በሁለት ወሳኝ የሆኑ የፖለቲካ ክስተቶች የሚወሰን ይሆናል።

ኣንደኛ፣ ከፌደራሊዝም ኣስተሳሰብ ኣልፎ የመገንጠልን ኣጀንዳ የሚያራምደው የኦሮሞ ነፃ ኣውጪ ግምባር (ኣነግ) ኦሮሚያ ውስጥ በሚያደርገው ኣጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ኣድረጃጀትና የፖለቲካ ብስለት የሚወሰን ይሆናል። ኦነግ በኦህዴድ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎች የያዙ ኣባላት እንዳሉትና የቄሮ እንቅስቃሴም በመዋቅሩ ስር ያለ እንደሆነ ሲገልፅ እንደቆየ ታሳቢ ማድረግ የሚሆነውን ለመገመት ይረዳል። ይህ በዚህ እንዳለ ብምዕራብ ኦሮሞያ፣ በተለይም በኣምቦ እና ኣካባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነውን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስም (ኦፌኮ) ከኦነግ ጋር ህብረት ወይም ውህደት ለመፈጸም በጥረት ላይ እንደሆነ መገንዘብም ኦህዴድ የቀረበለት ፈተና ቀላል እንደማይሆን እና ውሎ ኣድሮ ክእነዚህ ሃይሎች ጋር መተባበሩ የማይቀር ነው።

ሁለተኛ፣ የኦህዴድ የወደፊት ኣቅጣጫ በብኣዴን ዙሪያ እየተሰባሰቡ ያሉ የኣንድነት ሃይሎች በሚያራምዱት የፖለቲካ ኣቅጣጫ እና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይወሰናል። ይህ ጎራ ከላይ እንደተገለጸው የፌደራል ስርኣቱን፣ ህገመንግስቱን እና ክልሎችን ኣፍርሶ እስከ ማዋቀር የሚሄድ ኣስተሳሰብ ያለውና ኣንድ እግሩ በኣንድነት ሌላኛውም ጠባብ ብሄረተኞች የተከማቹበት ስብስብ በመሆኑ ኦህዴድን ጨምሮ ለኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች የማይመች እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ስለሆነም ኦህዴድ ኣሁን እየሄደበት ያለውን መርህ ኣልባ ግኑኝነትና የጎራ መደበላለቅ ሳይወድ ለማስተካከል የሚገደድበት ሁኔታ ይፈጠራል። ማለትም እነዚህ ሃይሎች በሚከተሉት የፖለቲካ መስመር እና በሚፈጠሩት ሁኔታውች ከምስጋት የተነሳ ኦህዴድ ወደ ነበረበት የፌደራሊስት ኣስተሳሰብ መመለሱ የግድ ሊለው ነው። በነገራችን ላይ ይህ ‘’የኣንድነት’’ እና የጠባብ ብሄርተኞች ጎራ ኣሁን እየሄደበት ባለውም መንገድ (ለምሳሌ ክልሎችን ኣፍርሶ ማዋቀር) ከቀጠለ ከኦህዴድ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቤንሻንጉል፣ ከትግራይ፣ ከኣፋር ክልሎች ጭምር የመጋጨት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ራሱ ድርጅቱም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግልፅ አያደርገው ይገኛል። ወጣም ወረደም ኦሮሚያ ውስጥ የመገንጠልን ኣላማ ያነገበው ኦነግ በነፃ በተንቀሳቀሰበት ሁኔታ ኦህዴድ የኣንደንት ሃይሎች እንደሚሉት ከፌደራሊዝም ኣስተሳሰብ ማፈንገጥም ሆነ ኣንቀፅ 39 ከህገ መንግስቱ የመሰረዝ ትግል ውስጥ ለመግባት ድፍረቱ ኣይኖረውም። እንዲያውም ኣሁን የተጀመረው የኦሮሞ ሃይሎች መሰባሰብ በሁለት የተቀራረቡ ሃይሎች ኣሊያም በኦነግ ጠቅላይነት ተገባዶ በኦነግ የተቦረቦረው ኦህዴድም ሳይወድ የውህደቱ ኣካል ሆኖ የጨዋታው ፍፃሜ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።

የተቀሩት ሁለቱ የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች፣ ማለትም ህወሓት እና ደህዴንም ፌደራሊዝም ኣራማጆች ሲሆኑ ዛሬ በኦህዴድና በብኣዴን ላይ የሚታየው የጎራ መደበላለቅ እና መርህ ኣልባ ግንኙነት የለም ወይም በዝቅተኛ ደረጃ የሚታይ ነው። በተለይም ህወሓት የኢህኣዴግን ድርጅታዊ ኣካሄድ እና ፕሮግራም የሙጥኝ ብሎ እየቀጠለ ያለ ድርጅት እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ነው። የኣቶ መለስ ዜናዊን የስድስተኛ ዓመት መታሰቢያ ቀንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከፍተኛ የህወሓት ኣመራር ኣባላት፣ ለምሳሌ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዝኣብሄር (ማንጀሪኖ) እንደተገለፀው ኢህኣዴግ ኣሁን ካጋጠመው ችግር ሊወጣ ከተፈለገ ያለው ኣማራጭ ወደ ነበረበት ህዝባዊና ኣብዮታዊ ኣስተሳሰብ መመለስ ነው ያለበት ማለታቸው የዚሁ ኣስተሳሰብ መገለጫ ነው (ቃል በቃል ኣይደለም)። ዓላማ ነውና ይህ ኣስተሳሰብም ሆነ የኢህኣዴግን ድርጅታዊ ኣካሄድ እና ፕሮግራም የሙጥኝ ብሎ መቀጠሉ በራሱ ክፋት የለውም፣ ስህተት ሊባልም ኣይችልም። ችግር ሆኖ የተገኘው ለሚፈጠረው ውስጣዊና ውጫዊ ኣዳዲስ ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ፍላጎቶች በሚመጥን ቁመና ዝግጁ ሆኖ ያለመገኘት ነው። በኣንድ የፖለቲካ ፕሮግራም ጥላ ስር ህብረት ፈጥረው የሚታገሉ ድርጅቶች ኣብረው ለመቀጠላቸው ምንም ኣይነት ዋስትና ስለሌለ ከተለመዱ ድክመቶች ለየት ያሉ ችግሮች ሲፈጠሩ ወይም ምልክቶች ሲታዩ እንደ ድርጅት ከችግሩ መውጫ የሚሆን ከተለመደው ለየት ያለ ኣቅጣጫ ሁሌም ዝግጁ ኣድርጎ መገኘት የኣንድ በሳል የፖለቲካ ድርጅት ተግባር ነው። ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ጉዳቱ ለሌሎችም ተርፈዋል። ወጣም ወረደም ህወሓት የፌደራል ሃይል ሆኖ እንደሚቀጥል ኣሁንም ግልፅ ኣድርገዋል።

ደህንዴንም ከዚህ የተለየ ሆኖ ኣልተገኘም። ኣቶ ሃይለማሪያም ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን ደህዴን እሳቸው ከስልጣን ሲወርዱ ሃላፊነት እና ሥነ ምግባር በጎደለው ኣካሄድ ድርጅቱ ለሁለት ከፍለዉት መሄዳቸው ይታወቃል። ኣንደኛው በተቃራኒያቸው የቆመው ክፋይ ሲዳሞዎች የበዙበት እና ከኣቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር የወገነ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ሃይለማሪያም የሚመሩት ኦህዴድን በመደገፍ ኣብይ ኣህመድን ወደ ስልጣን ለማምጣት የራሱን ሚና የተጫወተው እና ኣሁንም የመጀመሪያውን ክፋይ ከስልጣን በመግፋት ላይ የሚገኝ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል። በእንደዚህ ኣይነት ተቃርኖ ውስጥ የገባው ደህዴን ዛሬም ለኣቶ ሃይለማሪያም እና ኣብይ ኣህመድን በወገነው ቡድን እየተመራ ሲሆን የወደፊት እጣ ፈንታው በሁለት ነገሮች ሊወሰን ይችላል።

ኣንደኛው እና ጠቃሚው ጉዳይ የሲዳማ ህዝብ ራሱን የቻለ ክልል የመሆን ጥያቄ በቀላሉ የሚታጠፍ ስላልሆነ ደህዴንን በማስቀጠልና በማፈረስ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። እስከ ኣሁን ሲዳማ ክልል ስለመሆን ጉዳይ እያነሱ ያሉ ሃይሎች በደህዴን ያሉ ባይሆንም የሲዳማዎች ከደህንዴን መገፋት ውሎ ኣድሮ ክልል እንሁን ወደ ሚሉት ሃይሎች መገፋታቸው የማይቀር ነው። ይህ ሀገ መንግስታዊ መብት የተለየ መልክዓ ምድራዊና የህዝብ ይዘት ፈጥሮ የደህዴንን ፍፃሜ ሊያረጋግጥ ይችላል።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኣሁን ባለው የፖለቲክ ድርጅቶች ትርምስ እንደ ግንቦት ሰባት ኣይነት ድርጅቶች በዋናነት በደቡብ (በተለይም ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ወላይታ) የሚመራ በመሆኑ በተፈጠረላቸው ዕድል ገብተው በተጠቀሱት ቦታዎች/ህዝቦች ኣካባቢ የራሳቸው ተፅዕኖ ለመፍጠር ሰፊ ዕድል ኣላቸው። ጠ/ሚ ኣብይ ኣህመድ በኣሜሪካ ባደረጉት ጎዞ ስሙን ተሰምቶ የማይታወቀውን የጉራጌው ‘’ዘርማ’’ ደጋግመው ሲያሞካሹ የሰማናቸው እውነት ዘርማዎች ያደረጉት ኣስተዋፅኦ ስለነበር ሳይሆን ጉራጌው ብርሃኑ ነጋ ከሚመራው ግንቦት ስባት መዳፍ ላይ ሳይወድቅ ከወዲሁ ደህዴንን እየመሩ ካሉ ወ/ሮ ሙፍሪያት ካሚል ስር እንዲደራጁ በማሰብ እንደሆነ መገመት ኣይከብድም።

በኣጠቃላይ የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ኣሁን እየታየ ያለውን የተዘበራረቀ የፖለቲካ ኣቋም ኣጥርተው ግንባሩም በይፋ ኣፍርሰው ሁሉም ወደየ ጎራቸው የሚቀላቀሉበት ጊዜ ሩቅ ኣይሆንም። እስከ ኣሁን በኣሰራር ያፈረሱት ቢሆንም በኢህኣዴግ ምክንያት የመጣውን ስልጣን ድልድዩ እስኪሻገሩበት ድረስ ግንባሩን በይፋ ማፍረስ ኣልተፈለገም። በእርግጥ ጠ/ሚንስትሩ ኣንዴ ‘’ኢህኣዴግ የትም የለም’’ ሲሉ ኣስፈላጊ ሆኖ ስገኝ ደግሞ ‘’ኢህኣዴግ ከምን ጊዜ በላይ ጠንካራ ሆነዋል’’ በማለት እርስ በርሱ የሚቃረን ንግግር ሲያደርጉ እየሰማን ነው። የሆነ ይሁን በኣገራችን የፖለቲካ ምህዳር እንደ ተለመደው የፖለቲካ ድርጅት ብዛት የሚቀጥል ቢሆንም ቀጣዩ ጎዞ በዋናነት ፌደራልዝምን በሚቃረኑ የኣንድነትና ጠባብ ብሄርተኛ ሃይሎች ጎራ (ብኣዴን እና በዙሪያ ያሉ ሃይሎች) እና በፌደራሊስት ሃይሎች (የተቀሩት) የተከፈለ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ከላይ እነደተባለው የኦህዴድን ኣቋም ገና ለወደፊት የሚታይ ቢሆንም በሁኔታዎች ተገዶ ኣሁን ያለው ኣይነት የፌደራል ስርኣት ኣራማጅነቱን እንደሚቀጥልበት ሚዛኑ የደፋ ነው። ህወሓት እና ደህዴንም የፌደራል ስርኣት ከማራመድ ውጪ ያሳዩት ኣዲስ ኣቅጣጫ ባለመኖሩ በኣንድ ጎራ መቀጠላቸው የማይቀር ነው።

ይህ በእንዲ እንዳለ፣ ኣምስት ክልሎች እየመሩ ያሉ ኣጋር በሚል ስም የሚታወቁት ድርጅቶችም በዚህ የፌደራል ስርኣት ያገኙትን ራስን በራስን የማስተዳደር ስልጣን ኣሳልፈው ይሰጣሉ የሚል ግምት ስሌለ ኣዲስ በሚፈጠረው ሁኔታ ጎራቸው ከፌደራሊስት ሃይሎች ጋር መሆኑን ጥያቄ ውስጥ ኣይገባም። በዚህ ኣካሄድ ብኣዴን እና በዙርያው እያሰባሰባቸው የሚገኙት የኣማራ ብሄርተኛ ሃይሎች የፌደራል ስርኣቱን እና ብዝሃነትን እንደ ኣደጋ የሚመለከቱ ቢሆኑም በኣንድ ኣቅጣጫ ይፈሳሉ ተብሎ ኣይገመትም። እንዲያውም ካላቸው ውስጣዊ መከፋፈል እና ስር የሰደደ የሴረኝነት ባህል የተነሳ የተወሰኑትን በኣንድነት ጎራ የሚሰለፉ ሲሆኑ ሌሎቹ፣ በተለይም በከረረ የኣማራ ብሄርተኝነት የተደራጁ ሃይሎች ግን ኣንድ እግራቸው በኣንድነት ጎራ ሌላኛው ደግሞ የግዛት ማስፋፋትና በሌሎች ክልሎች የሚኖሩትን የብሄራቸው ተወላጆችን የጠበቀ ፖለቲካዊ ቁርኝንት የማድረግ ጉዳይ ታሳቢ ያደረገ የፌደራል ስረኣት እንዲኖር ያራምዳሉ የሚል ግምት ከፍ ያለ ነው። በኣጭሩ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በእነዚህ ሁለት ጎራዎች (ፌደራልሲት እና ኣንድነት የሚሉ በተግባር ግን ያልሆኑ) መካከል በሚደርግ ፍትጊያ ሲሆን ሂደቱ በሰላማዊ ከሆነ ኣገራችን የማስቀጠል ዕድል ይኖራል በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ ኣስከፊ እና ተመልሶ ሊጠገን የማይችል የመበተን ኣደጋ ሊያጋጥም ይችላል።

በተጨማሪም፣ በኢህኣዴግ ኣባልነትና በስልጣን ላይ የሌሉ ነገር ግን እንደ ዋዛ የማይታዩ ኦነግ እና ከኦነገ የወጡ ሃይሎች ሁሉ፣ ኦፌኮ፣ የኦጋዴኑ ኦኣብነግ፣ የሲዳማ ኣርነት ንቅናቄ (ሲኣን)፣ ኣገው ክልል መፍጠር የሚፈልገው የአገው ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኣዴፓ)፣ እና ሌሎች በመድረክ ስር የተሰባስቡ ድርጅቶች የፌደራል ስርኣት ኣራማጆች ሲሆኑ የመገንጠል ኣላማ ያነገቡም ይገኙባቸዋል። እነዚህ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኣቅጣጫ በመወሰን ረገድ ትርጉም ያላቸው ሃይሎች እንደሆኑ መረዳት ያስፈልጋል።
በመጨረሻም፣ እነዚህ ብተለይም በገዢው ፓርቲ እና በተነፃፃሪ ከበድ ያሉ ተፎካካሪ የመሆን ዕድላቸው ሰፋ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች የሚያደርጉት ቁርቁስ ከውጭ መንግስታት ተፅእኖ ነፃ ሊሆን እንደማይችሉ ከወዲሁ ብዙ ምልክቶች እያየን ነው። የFBI እና የኮንግረስ ኣባላት መጋበዝ ቀደም ሲል ተፈጥሮ የቆየውን ግኑኝነት ኣይነተኛ መገለጫ ነው። በኢሳያስ ኣፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግስትም በህጋዊ ኣተያይ የውጭ ኣካል ቢሆንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኣንድ የውስጥ ተቃዋሚ የበለጠ እንደሚንቀሳቀስና ኣንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይም (በገዥው ኢህኣዴግ ያሉም ጭምር) የጎላ ተፅእኖ እያሳደረ እንደሆነ መገንዝብ ኣስፈላጊ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኣካሄድ እና ኣቅጣጫ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እነዚህ ሃይሎች የሚጫወቱት ሚናም ከግምት ማስገባት ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ ኣይነት የተዘበራረቀ ሁኔታ ላይ ደርሰዋል። የሚሆነው መተንበይም ኣስቸጋሪ ነው። ከላይ የተዘረዘረው ሁሉ የሚሆነው ግን እንደ ኣገር የመቆየት ዕድሉ ካጋጠመን ብቻ ነው። እንደ ኣገር እንቆይ ይሆን? ኣሁን በተያዘው ከቀጥልን በእርግጥም ኣሳሳቢ ነው።
ቸር ይግጠመን