Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኤርትራውያን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍቅር ወድቀዋል! ከገብራይ

ኤርትራውያን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍቅር ወድቀዋል!
ከገብራይ
ለሃያ አመታት ሻክሮ የቆየውን የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ በኢሕአዴግ ተነሳሸነት የተጀመረው እንቅስቃሴ በአስደናቂ ፍጥነት ውጤታማ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዓብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሰላማዊ መፍትሔው የኤትራና የትግራይ ሕዝብ ግንኙነትን ባገለለ መንገድ እንዲፈፀም ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ በሁለት አገሮች ሕዝቦች አስገዳጅነት በመካከላቸው የተገነባው ኬላ ተደርምሷል፡፡ የኬላውን መደርመስ በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩት ሕዝቦች በተለያየ አቅጣጫ በመትመም ዓለምን ባስገረመ፣ ሁለቱን መሪዎች፣ በተለይም ደግሞ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ባስበረገገ አኳኋን ናፍቆታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኤርትና የትግራይ ሕዝቦች የሰሞኑ ግንኙነት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው ጠብ በሰላማዊ መንገድ እንዲዲፈታ ኢሕአዴግ ሲያራምደው የኖረውና፣ በቅርቡም ተነሳሽነቱን መውሰዱ ትክክል እንደነበር በተግባር አረጋግጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዓይናቸው ደም እየለበሰም ቢሆን ከመስከረም 1 ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ወደ ኤርትራ በመሻገር በህይወት ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ይጠይቃሉ፣ በህይወት የሌሉትን ደግሞ አልቅሰው እርማቸውን ያወጣሉ፡፡ የኤርትራ ተወላጆችም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አስመራን ጨምሮ የኤርትራ ከተሞች ከኢትዮጵያ በሚሄዱ እንግዶች ተጥለቅልቀዋል፡፡ በየቀኑ በመቶዎች በሚቆጠሩ መኪኖች ኤርትራዊያን ወንድምና እህቶቻችን ወደ ትግራይ ይገባሉ፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች ተለያይተው በነበሩባቸው ዓመታት የተወለዱ ወይም ያኔ ሕጻናት የነበሩ ወጣቶች ሳይቀሩ የተፈጠረውን እድል ለመጠቀም በስፋት ይጎርፋሉ፡፡ ኤርትራውያን ወገኖቻችን የአገራቸውን ደምበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ መሬት ሲገቡ ጀምሮ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት አመራር ላይ ያለውን ልዩነት በግልፅ ማጤን እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡
በኢሳያስ ትዕዛዝ በመድፍ ሳይሆን በደማሚት እንድትፈራርስ ተደርጋ የነበረችውን ውቢቷን ዛላንበሳ አልፈው አዲግራት ሲደርሱ የሚያዩትን ማመን ያቅታቸዋል፡፡ አዲግራት ከተማ በሃያ ዓመታት ውስጥ ትላልቅ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲ፣ የደራ ገበያ የሞላባትና ፎቅ በፎቅ ሆና ሲመለከቷት ከሚሰማቸው አድናቆት ባሻገር በአገራቸው ያለው ስርዓት ምን ያህል ወደ ኋላ እንዳስቀራቸው በመገንዘብ ቁጭት ያሳድራሉ፡፡ አዲግራትን አልፈው ውቅሮ ከተማ ሲደርሱ መቐለ የገቡ እስኪመስላቸው ድረስ የውቅሮ እድገት ሌላ አድናቆት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ከውቅሮ በኋላ ያለውን የአንድ ሰዓት መንገድ በሚያዩት ሁሉ እየተገረሙ ተጉዘው ሞሰቦ አፋፍ ላይ ብቅ ብለው መቐለን በርቀት ሲያዩ ደግሞ ሌላ ትንግርት እንደሆነባቸው አጫውተውናል፡፡
በአሁኑ ወቅት መቐለ ከተማ በሁሉም የከተማዋ መንገዶች፣ በገበያ ማእከሎችና ሆቴሎች መኪና ማቆሚያዎች ER የሚል ታርጋ ያላቸው መኪኖች ሲንቀሳቀሱና ቆመው ይታያሉ፡፡ በመጠጥና ምግብ ቤቶች እንዲሁም በመዝናኛ ቦታዎች ኤርትራውያንና ትግራዋዮች አንድ ላይ እንደቤተሰብና ጓደኛሞች አብረው ሲበሉና ሲጠጡ ይስተዋላል፡፡ ይህም ሁሉቱ ሕዝቦች ምን ያህል ተነፋፍቀው እንደኖሩ በግልፅ ያመለክታል፡፡ ኤርትራውያን መቐለ ውስጥ የሚያዩትና የሚሰሙትን ማመን እየተሳናቸው አንድን ጥያቄ ለተለያዩ ሰዎች ደጋግመው ይጠይቃሉ፡፡ መቐለ ውስጥ ያሉት ትላልቅ ሆቴሎች፣ የሚያማምሩ ፎቆች፣ ዘመናዊ የንግድ ማእከሎች…. የማን ናቸው የሚለው አንዱ ጥያቄያቸው ነው፡፡ የግለሰብ ባለሃብቶች ነው የሚል መልስ ሲያገኙም፣ እንዴት ይሆናል? የዚህን ያህል ሃብት የሚያፈራ ባለሃብት ከየት መጣ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ከሁሉም የሚያገኙት መልስ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ “ማንኛውም ዜጋ በፈለገው የሥራ መስክ፣ ያለ አንዳች ገደብ እንዲሰማራና ሃብት እንዲያፈራ ይበረታታል፤ ሃብቱን እንዲያሳድግና ራሱን ጠቅሞ አገርን እንዲጠቅም የባንክ ብድር፣ የመሥሪያ ቦታና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎች በመንግሥት ይደረግለታል፤” የሚል፡፡
ኤርትራውያን ወንድም እህቶቻችን ለሚያቀርቡዋቸው ጥያቄዎች የሚያገኙት መልስ እንዲሁም የከተማው እድገትም እያስገረማቸው የሚያዩትን ሁሉ በሞባይላቸው ፎቶ እያነሱ የመጎብኘት እድል ላለገኙት ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው በface book መልዕክት ይልካሉ፡፡ በመዝናኛ ቦተዎች ከሚያገኙዋቸው የመቐለ ነዋሪዎች ጋር ለመግባባት ደቂቃ አይፈጅባቸውም፣ በቀላሉ ይተዋወቃሉ፣ ስልክ ይለዋወጣሉ፣ የከረመ የሚመስል ጓደኝነት ይፈጥራሉ፡፡ ቢራ አዘው አስተናጋጆች ምን ዓይነት ቢራ ብለው በመጠየቅ፣ ዳሽን፣ ራያ፣ ዋልያ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሐበሻ፣ ሜታ፣ በደሌ፣ ሐረር….ወዘተ. የሚል ዝርዝር ሲነግሩዋቸው፣ ይህ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረት ነው ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በአገር ውስጥ ብዙ ዓይነት ቢራ የሚመረት መሆኑን እያስገረማቸው፣ ከሁሉም አንድ አንድ በማዘዝ በዙር ሁሉንም ይቀምሳሉ፡፡ የከተማው ነዋሪዎች “እንኳን ለመተያየት አበቃን” እያሉ ስለሚጋብዙዋቸውም የመቐለ ቆይታቸውን በእጅጉ ወደውታል፡፡
ከሁሉ በላይ የወደዱትና በእጅጉ ያጣጣሙት ግን መቐለ ውስጥ ያገኙትን ነፃነት ነው፡፡ በየትኛውም የከተማው ማእዘን ሲንቀሳቀሱ፣ “ማነህ? ወደየት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቃቸው፣ በዚህ ግባ በዚህ ውጣ የሚላቸው ወደሌለበት አገር መምጣታቸውን እንደ ተአምር ያወሩታል፡፡ የኤርትራ መንግሥት በነጋ በጠባ ወያነ እያለ ስለኢትዮጵያና ትግራይ ሕዝብ ይነግራቸው የነበረው ፕሮፖጋንዳ ምን ያህል የተሳሰተ አስተሳሰብ እንዲይዙ አድርጓቸው እንደነበር በፀፀት ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል አንዳችም ቂምና ጥላቻ እንደሌለ በተግባር መማራቸውን ይመሰክራሉ፡፡ በአጠቃላይ የተሰማቸውን ደስታ፣ በሚያዩት ለውጥ ሁሉ ያሳደሩትን አግራሞት ተናግረው መጨረስ አልቻሉም፡፡ ቆይታቸውን መጥገብ አቅቷቸዋል፡፡ ከኤሌክትሮኒክስና ከብርድ ልብስ ውጭ በሁሉም ዓይነት የፍጆታ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ የግንባታ እቃዎች…. ዋጋ መቐለ ርካሽ መሆን ብቻ ሳይሆን የፈለጉትንም ያህል ማግኘት ስለሚቻል ሁሉም የሚችሉትን ያህል ሲሸምቱ ሰንብተዋል፡፡
ኤርትራውያን እህት ወንድሞቻችን ከደስታና አድናቆታቸው ጎን ቅር የተሰኙባቸውን ነገሮችንም ከመግለፅ አልተቆጠቡም፡፡ ሁሉም “ ይህ ሰላም ለምን ቀደም ብሎ አልመጣም? እስካሁን ለምን ዘገየ?….” ይላሉ፡፡ “እናንተ ሃያ አመት ሙሉ ስትለሙ፣ እኛ ደግሞ ስንቆረቁዝ ኖረናል፣ ልታግዙን ይገባ ነበር” የሚል ወገናዊ መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ የመቐለ ከተማን በሚመለከትም “ይህንን የመሰለ እድገት ይዛ፣ የመንገድ መብራቶች ደካማ ናቸው፣ የአንድ ከተማ ውበት የምሽት ደማቅ መብራት ሆኖ እያለ መቐለ ግን መብራቶቿ ፈዛዛ መሆናቸው ቅር ብሎአቸዋል፡፡ አልፎ አልፎም “የሌብነት ችግር አጋጥሞናል፣ መኪኖቻችንን ውስጥ የተውነው ንብረት በር በመክፈት ተሰርቀናል፣ አምነን ያቀረብናቸው አንዳንድ ወጣቶች አጭበርብረውናል….” በሚል በግልፅ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ኤርትራውያን ከዛላንበሳ እስከ መቐለ ድረስ ያለውን በመመልከት የተሰማቸውን አድናቆት ደጋግመው በገለፁ መጠን፣ አብረው እዚህ እድገት ሲመዘገብ፣ እነሱ ወደ ኋላ ለመጎተታቸው ዋናው ምክንያት በሁለቱ አገሮች ያሉት ስርዓቶት ልዩነት መሆኑን ለመገንዘብ አስረጅ አላስፈለጋቸውም፡፡ እዚህ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመራ ስርዓት፣ እዛ በአንድ ግለሰብ ፍላጎት የሚመራ መንግሥት ምን እንደፈጠረ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በአንዱ የኢትዮጵያ ጫፍ ላይ ባዩት ብቻ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን የአመራር ውጤት ከልብ አድንቀዋል፡፡ ደሴ፣ ኮምበልቻ፣ ደብረብርሃን፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሓዋሳ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባን…. ወዘተ. የመጎብኘት እድል ቢያገኙ ደግሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ተአምር ሠሪነት ይበልጥ ይገነዘቡ ነበር፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ እንዲሉ ግን ትግራይ ላይ ባዩት ብቻ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ውድድ አድርገውታል፡፡ “ወያነ ንኢትዮጵያ አብሪስዋ ኢሎምና፣ ወያናይ ዴሞክራሲ ዓዲ ሓናፃይ እምበር፣ ዘፍረስ ከምዘይኮነ በዓይንና ሪእና”፤ “ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን እንዳልነበረች አድርጓታል ሲሉን ቢኖሩም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አገር ገንቢ እንጅ አፍራሽ አለመሆኑን በዓይናችን አይተናል” ብለዋል፡፡ ከወዲሁ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍቅር ወድቀዋል፡፡
የኤርትራ ወገኖቻችን በጥቂት ቀናት ቆይታ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትሩፋትን እንዲህ ሲያጣጥሙ፤ የወቅቱ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና ፅንፈኞች አገራችን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ በመመራት ዓለምን ያሰደነቀ እድገት ማስመዝገቧን በመካድ፣ “27 የጨለማ ዓመታት” እያሉ ውግዘት ያሰማሉ፡፡ ምንነቱን በግልፅ ባይነግሩንም “በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መቃብር ላይ አዲስ ስርዓት እንገነባለን” የሚል መፈክር ያስተጋባሉ፡፡ አቅጣጫው ወደማይታወቅ ጉዞ ሊመሩን ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተሠሩት መልካም ሥራዎች እንዲታቀቡ፣ የተፈፀሙ ስህተቶች ደግሞ እንዲታረሙ ይፈልጋሉ፣ ይህ እንዲሆንም ይታገላሉ፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን ገምግሞ፣ በፈፀማቸው ስህተቶች ራሱን ከልብ ወቅሶ፣ በህዝብ ላይ በደረሰው ጉዳት ይቅርታ ጠይቆ ለለውጥ መነሳቱን ይቀበላሉ፡፡ የታረመና እንዳለፉት አመታት ሁሉ የሕዝቡን ጥቅም የሚያረጋግጡ ተግባራትን የሚያከናውን ኢሕአዴግን ይሻሉ፡፡ ኤርትራውያን በሚገባ ሳያውቁት በአጭር ጊዜ በፍቅሩ የወደቁለት አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ መቸም ቢሆን እንደ መዳብ የማይቆጥሩት፣ በእጃቸው ላይ ያለ ወርቅ መሆኑን ይገነዘባሉ፡፡

መስከረም 12/2011