Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የክልሉ ህዝብ በተለይም ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ መጠበቅ አለበት- አቶ ለማ መገርሳ


አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ህዝብ በተለይም ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አሳሰቡ።

በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ያለው የጨፌ ኦሮሚያ 8ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው እለትም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው።

በጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳም በክልሉ ባሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ለጨፌው አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በክልሉ ባለው የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ ላይ በሰጡት ማብራሪያም፥ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በኦሮሞ ስም የተደራጁና መቀመጫቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች መግባታቸውን አንስተዋል።

ሆኖም ግን ጥሪ እየቀረበ ባለበት ሰዓት ከዚህ በተለየ አቅጣጫ የሚቆሙ እና የገንዘብ ድጋፍ እያገኙ ያሉ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ በግለሰብም በቡድንም ደረጃ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ አካላት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

ይህ ሁኔታም በተጨባጭ በኦሮሚያ ክልል ምእራቡ ክፍል ላይ መታየቱን ነው ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ ያነሱት።

የክልሉ ወጣት ከዚህ ቀደም መብቱን ለማስጠበቅ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ሲታገል መቆየቱን ያወሱት አቶ ለማ፥ በአሁኑ ወቅት ግን የክልሉን ወጣት ስም (ቄሮ) የሚለውን ስም በመጠቀም ዝርፊያ እና የፀጥታ ሀይሎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑንም አንስተዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ በተለይም ወጣቱ ይህንን በመከላከል የህግ የበላይነትን ሊያስጠብቅ እንዲገባም አቶ ለማ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትም ከተግባራቸው የማይቆጠቡ ከሆነ፥ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ይገደዳል ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ወሰን ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶችን አስመልክቶ ለጨፌው አባላት በሰጡት ማብራሪያም፥ አብዛኛዎቹ ግጭቶች በፕሮፖጋንዳ የተፈጠሩ ናቸው ብለዋል።

ይህም የክልሉ መንግስት የተፈጠሩ ችግሮችን ማርገብ ላይ ተጠምዶ ፊቱን ወደ ልማት እንዳያዞር የሚፈልጉ አካላት ስራ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

የክልሉ ህዝብን ይህንን አውቆ ተግባሩን ሊከላከል ይገባል ነው ያሉት።

የስራ አጥነትን አስመልክቶም፥ በክልሉ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር በማእድን ዘርፍ ላይ ብቻ በማሰማራት መፍታት አይቻልም ብለዋል።

የስራ አጥነት ችግርን በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ሰፋፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ወደ ክልሉ በመሳብ ነው ሲሉም አቶ ለማ ገልፀዋል።

አሁን በክልሉ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ትንንሽ ነገሮችን በመቆስቆስ ኢንቨስትመንት እንዳይበረታታ የሚያደርጉ አሰራሮች መቆም አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።

ሰፋፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ወደ ክልሉ ለመሳብ የሚያስችሉ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ ለማ አሳስበዋል።

የወረዳ በጀት ምደባን በተመለከተም፥ ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ ወረዳዎች የራሳቸው በጀት ተመድቦላቸው እንዲጠቀሙበት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።

ሆኖም ግን በተደረገው ማጣራት አብዛኛው ለወረዳዎች የሚለቀቀው በጀት ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ለደመወዝ ተከፋፍሎ ያልቃል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ይህንን ችግር ለመፍታት የክልሉ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አማካኝነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

በፐብሊክ ሰርቪስ በኩልም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።