Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኢትዮ-ኤርትራ ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጎን እንደሚቆሙ አረጋገጡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2010 (ኤፍቢሲ) የኢትዮ-ኤርትራ ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የትግራይ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጎን እንደሚቆሙ አረጋገጡ።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ዛሬ የተፈረመውን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት አስመልክቶ የትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫ አውጥቷል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታን በዘላቂነት ለመፍታት በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የቀረበውን ወሳኔ ተከትሎ ህወሓትና የትግራይ ክልል መንግስትም በተመሳሳይ አኳኋን የትግራይ እና የኤርትራ ህዝቦች ወንድማማችነት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ጠንክረው እንደሚሰሩ መወሰናቸውንና ውሳኔያቸውም ለመላው የትግራይ ህዝብ፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ለኤርትራ ህዝብ ይፋ ማድረጋቸውን መግለጫው አስታውሷል።

መግለጫው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የሁለቱ ህዝቦች ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት እያሳዩት ያለው ዝግጁነትና ተነሳሽነት የክልሉ መንግስት እንደሚያደንቅ አስታውቋል።

በተለይ የኤርትራ ህዝብ ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ሁኔታ በመፍታት የአትዮ-ኤርትራ ወንድማማችንትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ያሳየው ፍላጎት፣ ጉጉትና ፍቅር እጅግ የሚያስደስትና ከፊት ለፊታችን ብሩህ ተስፋ እንዳለም የሚገለፅ ነው ብሏል።

በመሆኑም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለኤርትራ ህዝብ ያለው ወንድማዊ አድናቆት ከፍ ያለ መሆኑን መግለፅ ይፈልጋል ነው ያለው።

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የተጀመረውን ሰላም የማረጋገጥ ስራ ይበልጥ ለማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀጥተኛ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመጀመር ወንድማማችነታቸውንና ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪው አቅርቧል።