Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ሁለት የብአዴን አመራሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በደብረ ማርቆስ መፈጸሙ ተሰማ

ሁለት የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከፍተኛ አመራሮች ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ሙከራ በደብረ ማርቆስ ከተማ መፈጸሙ ተሰማ።

የጥቃት ሙከራው የብአዴን መስራችና የቀድሞ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ በረከት ስምዖንና ሌላ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በሆኑት አቶ ምግባሩ ከበደ ላይ መሆኑን ከክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሁለቱ የብአዴን አባላት በከተማው ታይተዋል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ድረ ገጾች መናፈሱን ተከትሎ፣ ግለሰቦቹ ለሌላ ተልዕኮ እየተንቀሳቀሱ እንደሆኑ የጠረጠሩ የከተማው ነዋሪዎች በደብረ ማርቆስ ሆቴል ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ትኩረት ከተደረገባቸው ፖለቲከኞች የአንዱ ነው ተብሎ የተጠረጠረ ተሽከርካሪ በእሳት ማቃጠላቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ንጉሡ ድርጊቱን ያወገዙ ሲሆን፣ በከተማው ታይተዋል ከተባሉ አመራሮች አንዱ አቶ ምግባሩ በባህር ዳር የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አብረዋቸው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

‹‹ማንኛውም አመራርም ሆነ ዜጋ በየትኛውም ቦታ የመንቀሳቀስ መብቱን ሊገድብ የሚችል ነገር ሊኖር አይገባም፤›› ያሉት አቶ ንጉሡ፣ ‹‹ሰሞኑን የአንዳንድ አመራሮች ስም እየተጠቀሰ ሕዝቡን በማደናገርና ብጥብጥ በማንገስ በክልላችን የተገኘውን ሰላም ለመቀልበስ የሐሰት መረጃዎች እየተናፈሱ በመሆኑ ሕዝባችን ታላቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል፤›› ሲሉ አሳስበዋል።

ሁለቱ የብአዴን ፖለቲከኞች ለራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት በደብረ ማርቆስ ከተማ በድብቅ ሕዝብ በማወያየት ላይ እንደሚገኙ የሚገልጽ ሐሰተኛ ወሬ የጥቃቱ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።