Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ሁሉም ክልሎች ቅድሚያ ሰጥተው ሊወያዩበትና ግልፅ ኣቋም ሊይዙበት የሚገባ ጉዳይ, ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ ሰኔ 2010 ዓ/ም

ሁሉም ክልሎች ቅድሚያ ሰጥተው ሊወያዩበትና ግልፅ ኣቋም ሊይዙበት የሚገባ ጉዳይ

ይህ ኣጭር መጣጥፍ በዚህ ወቅት በኣገራችን ተፈጥሮ ያለው ውጥንቅጡ በወጣው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ኣንዳንድ ጎልተው የሚታዪ የህገ መንግስት ጥሰቶችና ኣሳሳቢነታቸው ለመጠቆም ያክል ነው። ይህ ኣርእስት ሰፊ የህግ ትንታኔ የሚያስፈልገው ሲሆን ሁሉም ክልሎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ያገባኛል የሚሉ ኣካላት እና ያገሪቱ ዜጎች ብልሽቱ ብዙ ርቀት ሳይጓዝና ለማረም የሚያስቸግርበት ደረጃ ሳይደርስ በኣፅንኦት ሊወያዩበትና ፈር ሊያሲይዙት የሚገባ ጉዳዩ በመሆኑ ለጥቆማ ያክል ኣጠር ያለ መነሻ ሃሳብ እንደሚከተለው ኣቅርቢያለሁ።

፩ኛ፣ በኣንዳንድ ክልሎች፣ በተለይም በኣማራ ክልል ግልፅ የሆነ የህገ የመንግስት ጥሰት ብቻ ሳይሆን ኣብሮነትን እና የኣገር ኣንድነትን የሚጎዳ ተግባር እየተፈጸመ ነው። ለምሳሌ እየተፈጸሙ ያሉ ዘር ተኮር ትንኮሳዎች እና የጠላትነት እወጃ ትተን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት እውቅና የሰጠውን ሰንደቅ ዓላማ በኣደባባይ በመቀዳደድ በኣገሪቱ የሚገኙ ብሄር ብሄረስቦች እና ህዝቦችን የጨፈጨፉና በኣለም ፊት ኣገሪቱንና ህዝቦችዋን ያዋረዱ ስርኣቶች ሲጠቀሙበት የነበረው ባንዴራ መጠቀም ኣንድ የህገመንግስት ጥሰት ማሳያ ነው። ክልሉ ኣብሮ ያፀደቀውን የጋራ ህገመንግስት መጣስ ማለት በትንሹ የሚያሳየው ክልሉ የኣገሪቱ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ተቀብለው ካፀደቁት የጋራ ቃል ኪዳን ኣፈንግጦ ተቃራኒ መንገድ እየሄደ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። እዚህ ላይ የክልሉ ህዝብ ለራሱ ክልል ብቻ የሚያገለግል ሰንደቅ ኣላማ የመምረጥ ህገመንግስታዊ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የኣገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ግን በሁሉም ክልል ህዝቦች በጋራ የሚወሰን ስለሆነ ኣንድ ክልል ብቻውን እንዳሻው እየተነሳ የመቀየር መብት የለውም። በነገራችን ላይ ዶ/ር ኣብይ በጠ/ሚንስትርነት ሲሾሙ እና በፓርላማው ፊት ቃል ሲገቡ ከፊተኛው ጠ/ሚኒስተር የተረከቡት ሰንደቅ ዓላማ ህገመንግስቱ የሚያውቀውን ባለ ኮኮቡ እንደነበር ልብ ይለዋል።

፪ኛ፣ ህገመንግስት ይጠብቃል፣ ይከላከላል። (በህገመንስቱ ኣንቀፅ 51 ቁ፣ 1 ) የተባለው የፌደራል መንግስትም በክልሎች የውስጥ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ጣልቃ ሊገባ እየመኮረ እንዳለ ሁሉም የሚያየው ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ጠ/ሚንስትሩ በክልሎች የውስጥ ጉዳይ ላይ ቀጥታዊ እና ቀጥታዊ ባልሆነ መንገድ ተፅእኖ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። ከህግ ኣንፃር ሲታይ ኣሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ ፓርቲው (ኢህኣዴግ) በግምገማ ወቅት ወሰኖበታል እየተባለ ባለፉት ሶስት ወራቶች የፈጸሙዋቸው ተደጋጋሚ የህገ መንግስት ጥሰቶች ብዙ ዜጎች ሲያነሱት የቆየ ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን በክልል በሚተዳደሩ ሚዲያዎች ላይ የሚያደርገው ትእዛዝና ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ ኣይነቱ የህገ መንግስት ጥሰት ዞሮ ዞሮ ከስርኣቱ ባህርይ የሚመነጭ ስለሆነ ሁሉም የፌደራል ተቋሞች ተመሳሳይ ጥሰት ለማድረግ እንደ ኣቅጣጫ ይዘው መስራታቸው ኣይቀርም። እንደሚታወቀው በቅርብ ኣመታት በኣጋጠመው ቀውስ እና ቀደም ሲል በነበሩ ኣመታት በብዙዎች ዘንድ ሲነሳ ከነበረው ጉዳይ ኣንዱ የፌደራል መንግስቱ እጁ እያስረዘመ ክልሎች ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን እውነተኛ የፌደራል ስልጣን ተጠቃሚ ሊሆኑ ኣልቻሉም የሚል ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ሲነገር የነበረ ጉዳይ ነው። ያንን ሁኔታም ጭምር ለመቀየር ታሃድሶ ተደርጎ ሲያበቃ የህገ መንግስት ጥሰቱም ሆነ ጣልቃ ገበነቱ ኣሳሳቢ እየሆነ መጥተዋል።

፫ኛ፣ ሌላው ህገ መንግስታዊ ስርኣቱ ከነኣካቴው ኣፍርሶ እና ክልሎችን እንደገነና ለማዋቀር ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳዩ ንግግሮች በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። ጠ/ሚንስትሩ ደጋግመው እንደሚሉት ‘’ክልል ድንበር ሳይሆን ወሰን ነው ያለው። በመሆኑም ዜጎች በፈለጉት ክልል ሄደው የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ኣላቸው።’’ በ’’ድንበር’’ እና ‘’ወሰን’’ ያለውን የቃላት ትርጉም ጨዋታ ትተን የመጀመሪያው ኣባባል ሁለተኛውን ኣባባል እስካገለገለ ድረስ ትክክል ነው ብለን እንወስዳለን። ሆኖም ግን ይህ ኣካሄድ ክልሎችን ኣፍርሶ እንደ ኣዲስ ለመስራት ከሆነ እየታሰበ ያለው እጅግ ኣደገኛ እና ኣገሪቱን የሚያፈርስ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለሆነም ለጊዚየው ብእጃችን ያለው መተኪያ የሌለው ኣማራጭ ክልሎች ባሉበት ቅርጽና የፌደራል ስርኣት በማቆየት መልካም ኣስተዳደር፣ ፍትህ፣ ልማት እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ኣንድነት እንዲኖር ጠንክሮ መትጋት ነው።

በታሪካችን እንደተመዘገበው የኣገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከድተው ሌሎች ብሄሮችን በሃይል በመደፍጠጥ በኣንድ የብሄር ማንነት፣ ኣንድ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ወግ ስር ለማዋሃድ (assimilation) በተደረገ ጭካኔ የተሞላበት ሙከራ ለዘመናት በኣሃዳዊ ስርኣት ሲነዱን በኖሩና በህዝቦች መካከል በተፈጠረው ደም ኣፋሳሽ ትግል ኣገሪቱ ከገደል ኣፋፍ ላይ መመለስዋን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። እዚህ ላይ ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባ ነገር ቢኖር በኣገሪቱ የሚታየው ያለው ዘር ተኮር ግጭት እና የከፋ ዘረኝነት ዋና ምንጩ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ኣከላለል ያመጣው ሳይሆን በዋናነት የብሄር ብሄረስ ሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ፈጽሞ ሊዋጥላቸው ባልቻሉ እና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ኣንድ ማንነት ማልበስ እና የኃላ ቀሩ ስርኣት መመለስ የሚፈልጉ ሃይሎች የሚደረግ ሃላፊነት የጎደለው ቅስቀሳ ሲሆን የነሱ ቅጥያ የሆኑ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መገናኛ ብዙሃን በሚረጩት መርዛማ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ነው።

በመሆኑም በኣገሪቱ የሚታየውን የጥላቻ ኣረምና እና ስር የሰደደ ዘረኝነት ነቅለን ለመጣል እና የኣገሪቱን ዘላቂ ልማት፣ ሰላም እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኣንድነት መፍጠር የምንፈልግ ከሆነ ዘላቂነት ከሌለው ህዝበኝነት በመራቅ በኣገሪቱ የህግ የበላይነት እና በሁሉም ደረጃ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ የግድ ይላል። የህግ የበላይነት እና ተጠያቂነት የሌለው ስርኣት የኣገርን ህልውና

የማስጠበቅ ችሎታው እጅግ የወረደ በመሁኑ ሄዶ ሄዶ ኣደጋ ላይ መውደቁ ኣይቀሬ ይሆናል። ስለሆነም የመንግስትን ስልጣን የያዘ ማነኛውም ኣካል በተራው ቂም ለማወራረድ የሚጠቀምበት ሳይሆን የኣገሪቱን ሰላም፣ ልማት እና ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠቀምበት የማይገኝ ዕድል ኣድርጎ ማየት ይኖርበታል። ነገ ብን ብሎ በሚጠፋ ጊዚያዊ ሰልፍና ጭኸት ተሰክሮ ኣገሪቱን ወደ የማትወጣበት ችግር እንዳትገባ መጠንቀቅ ያሻል። የፌደራል መንግስቱ ዋና የስልጣን ምንጭ የሆኑት የክልል መንግስታትም ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚሉት ነገሩ ከእጃቸው ሳያመልጥ በፊት ህገ መንግስቱ እንዳይጣስ በፅናት መቆም ኣለባቸው እንላለን።

ቸር ይግጠመን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.