Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የደኢህዴን የከፍተኛና የመካከለኛ አመራሮች መድረክ ተጠናቀቀ


አዲስአበባ፣ ሰኔ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን የከፍተኛ እና የመካከለኛ አመራሮች መድረክ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።

በመግለጫው አርሶ አደሩን፣ የከተማ ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ላብ አደሩን፣ ምሁሩንና ልማታዊ ባለሀብቱን በህዝባዊ ውግንና በማገልገል ተራማጅነቱን ይበልጥ በተግባር ለማሳየት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጦ ስለመነሳቱ ድርጅቱ አስታውቋል።

በህዝቦች መካከል አለመተማመንን የሚፈጥሩ ማንኛውንም ዓይነት ጉድለቶች በማሻሻል የክልሉን ህዝቦች በተለያዩ መሰረተ ልማቶች በማስተሳሰር እና የጋራ የሆኑ እሴቶችን በማጎልበት ይበልጥ ስነ ልቦናዊ አንድነት እንዲጎለብት በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የበለጠ ለመገንባት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በልማቱ ተሳታፊ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆንና ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቋል።

አመራሮቹ ሁሌም ራሳቸውን ለክርክርና ሂስ ክፍት በማድረግ ከስህተት የሚማር መሪ በመሆን፣ በጥብቅ ድርጅታዊ ዲስፕሊን የአመራር ስነ ምግባር ህጉን በመጠበቅ፣ በተግባር ውጤታማ መሆንን መለያ በማድረግ፣ በአመለካከት ለአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርና ለህሊና በመታመን ጽኑ አቋም በመያዝ ራስን ከወቅታዊ የለውጥ ጉዞዎች ጋር በማጣጣም የድርጅታቸውን መርሆዎችና እሴቶችን ጠብቀው ለመሄድ ከምን ጊዜም በላይ ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በአፈፃፀም ወቅት የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ግንባር ቀደም ተዋንያኖች እንደሚሆኑ ገልጸው፥ በተለይም የታችኛውን አመራር አቅም ከመገንባት አኳያ የሚነሱትን የትምህርትና ስልጠና ዕድሎች አሰጣጥንና ሌሎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለቅሞ በማውጣት መፍትሄ እንዲያገኙ እንደሚደረግም በመግለጫው ተጠቁማል።

በተጨማሪም ክልላዊ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ በሁሉም የልማት መስኮች ትኩረት ሰጥቶ በርብርብ እንደሚሰሩ ድርጅቱ አስታውቋል።

ድርጅቱ ሰፊ የገበያ እድል እና ሌሎች ተያያዥ መልካም አጋጣሚዎች አንፃር ያልተጠቀመባቸው በርካታ እድሎች መኖራቸውን የገመገመ ሲሆን፥ በዚህም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለቅሞ በመያዝ የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የአደረጃጀትና አሰራር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተደረገ ባለው ጥናት መነሻ ፈጥኖ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ በክልሉ እያደገ የመጣውን የመልማት ፍላጎት በተገቢው ለማሟላት አመራሮቹ ተግተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የድርጅቱን ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ጨምሮ የህዝብ ም/ቤቶች፣ ብዙሃን ማህበራትን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሚዲያ ተቋማትን ከመደገፍ እና ከማብቃት አኳያ ያሉ ውስንነቶች በመቅረፍ ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ለክልሉ አዋሳኝ በሆኑት የሀገሪቱ ክልሎች ህዝቦች እና በክልሉ ህዝቦች መካከል የተፈጠሩትን የፀጥታ ችግሮች ጊዜ ሳይሰጣቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሚመለከታቸው ከፌዴራል እና ክልል መንግስታት ጋር በመቀናጀት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሌት ተቀን የሚረባረቡ መሆኑን አስታውቋል፡፡

መሪ ድርጅቱ ኢህአዴግ እና መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጀ እየወሰዳቸው ባለው የልማት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና የሰላም አጀንዳዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ክርክር በማድረግ በፖለቲካዊም ይሁን በኢኮኖሚ ማነቃቂያ የፖሊሲ ማሻሻያ ሀሳቦች ትክክለኛ እና ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ነው ያመለከቱት።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ጋር ተያይዞ ባለው ጉዳይ በቅርቡ መንግስት የወሰነውን ውሳኔ በማስመልከትም “እኛም የደኢህዴን አመራሮች ተቀብለን ከድርጅታችንና ከመንግስታችን ጎን በመቆም የሚጠበቅብንን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታችንን እያረጋገጥን ወደፊትም እንደ ኢህአዴግ በሚወሰኑ የጋራ አጀንዳዎቻችን ዙሪያ ከሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን ህግንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓትን በተከተለ አኳኋን ደኢህዴን የበኩሉን ሀገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን” ብለዋል በመግለጫቸው።