Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ወሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር ወሰነች


አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር አለመግባባት ለመፍታት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ተስማማች።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባው የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ነው ያለ ሲሆን፥ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ የመኖሪያ ቀዬ ማፈናቀሉን መግለጫው አስታውሷል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጦርነት በሀገራቱ ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፤ በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ነው ያለው መግለጫው።

በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አንስቷል።

ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ መፈጠሩን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በመግለጫው አንስቷል።

የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት 20 አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል ብሏል።

“እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም” ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሄ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው ብሏል።

ይህን ባለማድረጉም በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዋል ብሏል መግለጫው።

“የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን” ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ “በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን” ብሏል በመግለጫው።

በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን በመግለጫው አረጋግጧል።

የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጠይቋል።