Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ሰበር ዜና: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶ/ር አብይ አህመድን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶክተር አብይ አህመድን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው ከኢህአዴግ በእጩነት የቀረቡለትን ዶክተር አብይ አህመድን ሹመት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ ለህገመንግስቱ ታማኝ በመሆን ከሀገሪቱ እና ከህዝቡ የተጣለባቸውን ሀላፊነት በቅንነት፣ በታታሪነት እንዲሁም ህግ እና ስርዓቱን መሰረት በማድረግ ስራቸውን ለመፈፀም ቃል ገብትዋል።

በመቀጠለም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

በሀገሪቱ ታሪክ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰናባች እና ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በአንድ ላይ ተገናኝተው የስልጣን ርክክብም አድርገዋል።

abiy_haile_2.jpg

abiy_haile_4.jpg

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበረው ቆይታ እንደተጠናቀቀም ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀባበል ስነ ስርዓት በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።

በአቀባበሉ ላይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትም ጨምሮ የጠቅላይ ሚንስትሩ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸውም ተገኝተዋል፡፡

abiy_PM_office.jpg

የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፅህፈት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎችን አዘዋውረው አስጎብኝተዋቸዋል።

የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም፥ በቀጣይ ጊዜያት ዶክተር አብይን በሙሉ ልብ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቀላል የሚባል ኃላፊነት አይደለም ያሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም፥ መሰዋዕትነትን ለመክፈል ለተዘጋጀ ሰው ግን በቀላሉ ማለፍ ይቻላል ብለዋል።

ዋናው ኃላፊነት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቢሆንም፤ አስፈላጊውን ትብብር እና እገዛ ግን በማንኛውም ጊዜ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው፥ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ይህችን ሀገር ለመምራት ከባድ የሃላፊነት ጊዜን አሳልፈዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

አቶ ኃይለማርያም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረግም አርአያ መሆን እንደቻሉ የገለፁት ዶክተር አብይ፥ እሳቸውም በዚሁ መልኩ የስልጣን ሽግግር ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

ህዝብና መንግስት የሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንደሚሰሩ ነው የገለፁት።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብር አህመድ በዛሬው እለት በይፋ ስራቸውን ጀምረዋል።