Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባው በአመራሩ መካከል የአመለካከት አንድነት በተሻለ ሁኔታ ፈጥሮ መጠናቀቁን ኢህአዴግ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር በሚያጠናከር መልኩ በአመራሩ መካከል የአመለካከት አንድነት በተሻለ ሁኔታ ተፈጥሮ መጠናቀቁን ድርጅቱ ገለፀ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ከመጋቢት 2 እስከ 10 ቀን 2010 ዓም ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በብሄራዊ ድርጅቶች መካከል የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የአመለካከት አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በጥልቀት ተፈትሾ በመግባባት መጠናቀቁን ገልጿል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፈው ታህሳስ ወር ለ17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ ያስቀመጣቸው ውሳኔዎች በመመስረት በአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች የስራ አስፈጻሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴዎቻቸው የተከናወኑ የግምገማ ሪፖርቶችን በዝርዝር በመፈተሽ፣ ጉድለቶችና ጥንካሬዎያቻቸውን በመለየት በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ የአመራር ድክመቶች የወለዳቸው ችግሮችን ለማረም የሚያስችል የአመለካከት አንድነት የሚፈጥር ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጡን መግለጫው ጠቁሟል።

በዚህ ግምገማ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ሀገሪቱ ያስመዘገበቻቸው ለውጦች እና በሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎች በሚመርዋቸው ክልሎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አስተዋጽኦ በዝርዝር በመፈተሸ ጥንካሬዎቻቸው ጎልብተው እንዲቀጥሉ፣ ጉድለቶች ደግሞ በፍጥነት እንዲታረሙ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተመልክቷል።

ግንባሩና እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት በጽኑ መሰረት ላይ እየተገነባ ያለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመርና ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከጥቃት ለመከላከል የህዝብን ጥያቄ በአግባቡና በፍጥነት በመመለስ የተጀመረው የህዳሴ ጉዞን ለማስቀጠል እንዲቻል አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን ማጠናከርና ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ መላው የኢህአዴግ አመራርና አባላት በጽናት ሊታገሉት እንደሚገባ በማስመር ስብሰባውን እንዳጠናቀቀም ነው ያመለከተው።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባም በዛሬው ዕለት እንደሚጀመር እና በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተገምግሞ በቀረበለት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሪፖርት ላይ እና ለዕይታ በሚጠቅም ሰነድ ላይ ተወያይቶ በመጨረሻም የድርጅቱን የአመራር ክፍተት ያሟላል ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጫው አስታውቋል።

የአመራር ክፍተቱ የሚሟላው በኢህአዴግ ፕሮግራም፣ ህገ ደንብና በተለመደው የኢህአዴግ አሰራር መሰረት ይሆናልም ብሏል።