Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከመተማ ወደ ጎንደር ከተማ ሊገቡ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከመተማ ወደ ጎንደር ከተማ በድብቅ ሊገቡ የነበሩ 21 ሽጉጦችና ከ15 ሺህ በላይ ጥይት መያዙን በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ አስታወቀ።

በጎንደር ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ የሰራባ ኬላ አስተባባሪ ኮሎኔል ብርሃነ መብራት ለእንደተናገሩት፥ የጦር መሳሪያና ጥይቶቹ የተያዙት ከጭልጋ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሰራባ በተባለው የመቆጣጠሪያ ኬላ ነው።

የጦር መሳሪያዎቹንና የክላሽ ጥይቶቹን በድብቅ ጭኖ የተገኘው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-12155 አዲስ አበባ የሆነ ፒካፕ ተሸከርካሪ ሲሆን በመኪናው ውስጥ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከትናንት በስቲያ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በተደረገው ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ የተያዙት የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች በመኪናው አካል ላይ በረቀቀ መንገድ ተበይደው በተዘጋጁ ስውር ቦታዎች ተቀምጠው የተገኙ ናቸው።

“ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በአካባቢው እየተስፋፋ መጥቷል” ያሉት የኬላው አስተባባሪ፣ በዚህ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ወንጀለኞችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት ሕብረተሰቡ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ከታህሳስ እስከ የካቲት ወር 2010 ዓ.ም ባሉት ሦስት ወራት ብቻ በሰራባ ኬላ 7 ሺህ ጥይቶች፣ 25 ሽጉጦችና ሁለት ክላሽን ኮቭ ጠብመንጃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሎኔል ብርሃነ ተናግረዋል።