Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ሁከት ለመቆጣጠርና ሰላም ለማረጋገጥ የወሰዳቸውን እርምጃዎች እናደንቃለን – ሬክስ ቲለርሰን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2010(ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ትናንት ከኢትዮጵያ የጀመሩት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ዛሬ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ከውይይታቸው በኋላ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፥ በውይይታቸው ላይ ከሁለትዮሽ ጉዳዮች በተጨማሪም የደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን ጉዳይ ማንሳታቸው ተመልክቷል።

ዶክተር ወርቅነህ በመግለጫው ላይ ኢትዮጵያ እና አሜሪካን የበርካታ አመታት ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው፥ የዛሬው ጉብኝትም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግዋል ።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው አንስተዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ አጋር መሆኗን ያነሱት ዶክተር ወርቅነህ፥ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ይሰራሉ ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ የተከሰተውን ሁከት ለመቆጣጠር እና ሰላም ለማረጋገጥ በሀላፊነት የወሰዳቸውን እርምጃዎች እናደንቃለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታም ኢትዮጵያውያንን ብቻ የሚመለከት ነው ያሉት ሬክስ ቲለርሰን፥ አሜሪካ ግን የሀገሪቱን ልማትና ዴሞክራሲን የማረጋገጥ ስራ ትደግፋለች ነው ያሉት።

ወጣት በሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ውስጥ እየተከናወነ ያለው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የስልጣን ሽግግር አወንታዊ ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።

የሀገሪቱን ሁኔታ አሜሪካ እየተከታተለች መሆኑን የገለፁት ሬክስ ቲለርሰን መነግሰት የተለያዩ እስረኞችን ከእስር መፍታቱ ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለውን ጠቀሜታ አንስተዋል።

ዴሞክራሲ ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑም የሀገሪቱ ህዝቦችም ከረብሽ በመታቀብ ሂደቱን በትእግስት እንዲጠባበቁ ነው ያሳሰቡት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአጭር ጊዜ እንደሚሆን እና የሰብዓዊ መብት ባከበሩ መልኩ እንደሚተገበር እምነታቸውን ገልፀዋል።

ከዶክተር ወርቅነህ ጋር በነበራቸው ውይይት የፀጥታ ሀይሎች ያለ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰላምና ጸጥታን ሊያስከብሩ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲን አሜሪካ ትደግፋለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ የአሜሪካ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።